ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

***********************************************************

(የካቲት17/2015 ዓ/ም፤ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ/ም በመደበኛው መርሃ ግብር በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ የመጀመሪያ ዲግሪ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከባሕር ዳር ከተማና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች፤የጸጥታ አካላት፤የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የሰላም ምክር ቤት ኮሚቴ አባላት ጋር የተማሪዎችን አቀባበል በተመለከተ ውይይት አድርገዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች  ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ   እንደገለጹት  ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን በዚህ አመት  5,187 ተማሪዎች መርጠውታል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ይህ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አንጻር ሲዎዳደር በጣም ትልቅ  ቁጥር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ እንድንመረጥ ያደረጉንም በጣም ብዙ ምክኒያቶች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉ የመማር ማስተማር ስራዎች አቅምና ብቃት፤ የመልካም አስተዳደር ስራዎች፤ ዩኒቨርሲቲው  የሚገኝበት  ከተማ እና ማኅበረሰብ ሰላማዊ መሆን ከምርጫው ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው ብለዋል፡፡

ዶ/ር እሰይ ከበደ አክለውም  ባሕር ዳር እንደቤቴ መርሀ ግብርም ለአንድ አዲስ ተማሪ አንድ  የቃል ኪዳን  ቤተሰብ ከባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ልክ እንደ ቤተሰብ ሆኖ በቆይታቸው ተንከባክቦና ደግፎ  እንደቤታቸው  እንዲኖሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አራጋው ብዙዓለም በበኩላቸው ተማሪዎች አንድን  ዩኒቨርሲቲ ሲመርጡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከተማሪዎች ባሻገር የቤተሰብ ይሁንታም  ትልቁን  ቦታ ይይዛል፡፡ ቤተሰብ ስለ ዩኒቨርሲቲው መገኛ አካባቢ ያለው መረጃ እና የሚሰማው ስሜት በራሱ ትልቅ ድርሻ  ይኖረዋል፡፡  ባሕር ዳር ውበቷና ድምቀቷ እንደተጠበቀ ሆኖ ከተፈጥሮ ለሚዋደዱ ሰዎች እንደ ጣና ያለ መዝናኛ  ያላት፡፡ መንፈሳዊ ነገር ለሚያሻቸው ደግሞ ገዳማቷ አይጠገቡም ብለዋል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላትም በትኩረት በተማሪዎች ቅበላ ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አቶ አራጋው ብዙዓለም ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጸጥታና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ኢኒስፔክተር ሀብታሙ መለሰ እንደተናገሩት ተማሪዎች ደህንነትና ሰላምን ጠብቆ ቅበላውን ለማካሄድ የዩኒቨርሲቲው የጸጥታ አካላት ከሌሎች በከተማው ከሚገኙ የጸጥታ አካላት እና የፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን ዶ/ር በላይ ተፈራ ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ተማሪዎች የሚገቡባቸውን ግቢዎች የማሳወቅና የዶርም እና የአልጋ ድልድል እና ተያያዥ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋርም ተማሪዎችን በቅንጅት ለመቀበል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ጥበበ ሰሎሞን በበኩሉ ተማሪዎች የሚገቡባቸው የዘንዘልማና የግሽ ዓባይ ግቢዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ተማሪዎችን ለመቀበል ህብረቱ ከተማሪዎች ዲን ጽ/ቤት ጋር በመሆን እየሰራ ሲሆን አዲስ ተማሪዎችም ስለዩኒቨርሲቲው ህግና ደንብ እንዲሁም ስለግቢዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ዝግጅት ተደርጓል ብሏል፡፡

ለተጨማሪ መረጃዎች፡-

Facebook  https://www.facebook.com/bduethiopia 

YouTube    https://www.youtube.com/@bduethiopia

Instagram  www.instagram.com/bduethiopia 

TikTok       https://www.tiktok.com/@bduethiopia 

Telegram   https://t.me/bduethiopia 

Twitter       https://twitter.com/bduethiopia 

LinkedIn     http://www.linkedin.com/school/bduethiopia

Website     https://bdu.edu.et/

Facebook (https://www.facebook.com/bduethiopia)