በጦርነቱ ቆስለው ማገገሚያ ማዕከል ላሉ የሰራዊት አባላት

በጦርነቱ ቆስለው ማገገሚያ ማዕከል ላሉ የሰራዊት አባላት የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ

*********************************************************************

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ‹‹አሁንም ያስፈልጋል›› በሚል መንፈስ ተነሳስተው በጦርነቱ ቆስለው በፈለገ-ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል ማገገሚያ ክፍል ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት፣ልዩ ኃይል፣ፋኖ እና ሚሊሻ አባላት በ28/06/14 ዓ.ም የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህር አቶ ነጋ እጅጉ፣ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህር አቶ ብሩክ ገድፍ እና የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህር አቶ ይደግ ሙናና በጋራ በመተባበር 21‚970 (ሃያ አንድ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ) ብር፤ ከሶሻል ሳይንስ ፋኩልቲና ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማህበረሰብ ደግሞ 28‚000 (ሃያ ስምንት ሺ) ብር ከማርያም ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች መሰብሰባቸውን ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም መምህራኖች በተሰበሰበው ብር እስካሁን ማገገሚያ ክፍል ያሉትን የሰራዊት አባላት ችግር በመገንዘብ 150 ቁምጣና ቲሸርት፤117 ሙሉ ቱታ በመግዛት በፈለገ-ሕይወት ሬፈራል ሆስፒታል ለሚገኙ በጦርነቱ ለተጎዱ የሰራዊት አባላት አበርክተዋል፡፡

አልባሳቱን የተረከቡት የሎጀስቲክስ አስተባባሪ ኮሬኔል ተሾመ ጌጡ ሲሆኑ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ድጋፎችን ያበረከተ ምስጉን ተቋም መሆኑን ገልፀው አልባሳቱ እዚህ ላሉት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ቦታዎች ሆነው ህክምናቸውን ለሚከታተሉ የቆሰሉ የሰራዊት አባላትም ሆኑ በጦርነቱ ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊነቱ እየታየ የቅድሚ ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸውን በመለየትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለታለመለት ዓላማ እንደሚያውሉት አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሙሉጎጃም አንዱዓለም