'በጎነት ለአብሮነት' የበጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት

5ኛው ዙር ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት በስራ ዓመራር አካዳሚ አዳራሽ ተካሄደ ፡፡

ጥቅምት 27/2015ዓ/ም (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) በሰላም ሚኒስቴር እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትብብር ‹‹በጎነት ለአብሮነት›› በሚል መሪ ሃሳብ ከሁሉም ክልሎች ለተወጣጡ ከ2000 በላይ ወጣቶች ለ33 ቀናት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ ስልጠና ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት በስራ ዓመራር አካዳሚ አዳራሽ ተካሂዷል ፡፡   

በመርሃ ግብሩ የእንኳን መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ አብሮነት ለተለየ አላማ እና ለአዲስ ነገር ውል የምንይዝበት፣ የምንገናኘበት እንጂ የማንለያይበት፣ በጋራ ሆነን ለህዝባችን ለራሳችንና ለአገራችን የምንዘምት መሆኑን በማውሳት እንኳን ወደ ውቢቱ ባሕር ዳር በሰላም መጣችሁ ብለዋል፡፡  ‹‹በጎነት ለአብሮነት›› የሚለው ቃል ከበጎ ፈቃድ ጋር የተገናኘ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው፣ የስርዓተ ትምህርቱ አካል የሆነ አለምአቀፋዊና ኢትዮጵያዊም ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው በቆይታችሁ ለመጣችሁበት ዓላማ ( ስልጠናውን፣ መተዋወቁን፣ መረዳዳቱን፣ አብሮነት ምን ያህል እንደሚጠቅም ማወቅንና የዚህ አምባሳደር ሆኖ በህይወትም ኖሮ መስበክን ) ቅድሚያ በመስጠት እንዲሰሩ ለሰልጣኞች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳሕሉ ባሕር ዳር ከተማ ፍጹም ሰላማዊ፣ የብሔርም ሆነ የሀይማኖት ግጭት የማይስተዋልባት ከተማ ናት፡፡ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በትምህርት ሚንስቴር የሰላም ዩኒቨርሲቲ ተብሎ እውቅና የተሰጠው አንድም ቀን ለብጥብጥ ተቀባይም ሰጭም ያልሆነው ሰላም ወዳድ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ በመገኘቱ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ሚንስቴር የክብር ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ በጎነት ለአብሮነት በሚል መሪ ሀሳብ በሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የተጀመረው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ኢትዮጵያዊ እሴቶችን፣ መርሆዎችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ በዘር፣ በጎሳ በሀይማኖት እና በሌሎች ማንነቶች ላይ መሰረት አድርጎ ያለውን መከፋፈል ለማስወገድ ሚናው የጎላ ስለሆነ ለአገራችን በጅጉ አስፈላጊ ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡

አምስተኛው ዙር ለየት የሚያደርገው አገራችን ዘርፈ ብዙ ዋጋ ያስከፈላት እና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ የተደረገው ድርድር ኢትዮጵያ በምትፈልገው መልኩ ስምምነት ላይ በተደረሰበት እና እንደ አገር ኢትዮጵያውያን ባሸነፍንበት፣ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ መተግባር ባሳየንበት፣ የኃያላን እጅ ጥምዘዛ በማምከን የጥቁሮችን ዳግማዊ ድል ባበሰርንበት መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡ በዚህም አምስተኛው ዙር 10ሺ ሰልጣኞች ከመላው አገሪቱ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተመዘገቡ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በባሕር ዳር፣ በጅማ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በዋቻሞ እና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲዎች ስልጠናው የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የሰላም አምባሳደር ለሚሆኑ ወጣቶች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ዘውዴ ኤጄርማ በበኩላቸው ሰልጣኞች ለ33 ቀናት የሚቆዩ ሲሆን ወጣቱ አገሩን የሚወድ፣ ስነ መግባር ያለው፣ የስራ ባህል ያለው፣ ምክኒያታዊ የሆነ ወጣት እንዲፈጠር እና ለህብረተሰቡ የሚያገለግል ሆኖ እንዲወጣ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ፖሊስ ባንድ በደመቀው መርሃ ግብር የሰላም ሚኒስቴር አመራሮች፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ታድመውበታል፡፡