በዝቅተኛ የስራ መደብ ላይ ለሚገኙ ሰራተኞች ደረጃ ለማሻሻል ...

በዝቅተኛ የስራ መደብ ላይ ለሚገኙ ሰራተኞች ደረጃ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

***************************************************************

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዝቅተኛ የስራ መደብ ላይ ለሚገኙ ሰራተኞች እውቀት፤ ክህሎትና ደረጃ ማሻሻል የሚያስችል ስራ እየስራ መሆኑን ገለጸ፡፡

የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ  የአስተዳደር  ጉዳዮች  ም/ፕሬዚዳንት  አቶ  ብርሃኑ  ገድፍ  እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲዎች ምግብ ቤት የሚሰሩ ሰራተኞች በብዛት ማንበብና መጻፍ የማይችሉና በትምህርታቸው ብዙም ያልገፉ፣ ከ8ኛ ክፍል ያልዘለሉ በመሆናቸው የሰራተኞችን ደረጃ ለማሻሻል ተግዳሮት በመሆኑ ስልጠና አግኝተው COC መፈተን ነበረባቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለስልጠናው የሚያስፈልገውን ክፍያ በመክፈል እንዲሰለጥኑ አድርጓል፡፡ በመቀጠልም ለCOC ምዘና የሚያስፈልገውን ክፍያ በመክፈል እንዲመዘኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ስልጠናውን ለመውሰድ 467 ሰራተኞች የተመዘገቡ ሲሆን 8ቱ በተለያየ ምክንያት ስልጠናውን አላጠናቀቁም፡፡ 459 ሰራተኞች ስልጠናውን ጨርሰው አብዛኞቹ COCውን በብቃት አልፈዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ሰራተኞች ጥሩ እውቀትና ክህሎት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ የምግብ ቤት ሰራተኞች በተለይም እናቶች ሁልጊዜም ለዩኒቨርሲቲው የኩራት ምንጭ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው ኩራት ይሰማዋል፡፡ በሌሎች ዘርፎችም በቀጣይ እያሰለጠን ሰራተኞች ተመዝነው ደረጃቸው እንዲሻሻል ከማድረግ ባሻገር እውቀትና ክህሎታቸውም እንዲያድግ ለማድረግ እቅድ ተይዟል ያሉት ም/ፕሬዚዳንቱ ሌሎች የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችም ይህን እንደ ተሞክሮ ቢወስዱት መልካም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ስራው እንዲሳካ ብዙ ጥረት ላደረጉ የተማሪዎች አገልግሎት የስራ ሓላፊዎችም ምስጋና አቅርበዋል አቶ ብርሀኑ፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅሬ አልማው በበኩላቸው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ይሰራል ለአብነትም፡- ለተማሪዎች የምክር አገልግሎት፤ የምግብ አገልግሎት፤ የመኝታ አገልግሎት፤ ስፖርትና የመዝናኛ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለምግብ ቤት ሰራተኞች ስልጠና በመስጠት እየሰራ ያለው ስራ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በተለይም ለረጅም አመታት እንጀራ እየጋገሩ፤ ወጥ እየሰሩ ዩኒቨርሲቲውን ከዚህ ላደረሱት እናቶች ምስጋና ይገባል፡፡ ይህን ስራ ለማሳካት ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ጥረት ላደረጉት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ወ/ሮ ፍቅሬ፡፡

በቀጣይም በዝቅተኛ የስራ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰራተኞችን በማሰልጠን የተሻለ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው፤ ደረጃቸው እንዲሻሻል እንሰራለን ብለዋል ወ/ሮ ፍቅሬ አልማው፡፡

በዋናው ግቢ ወጥ ቤት የሚሰሩት ወ/ሮ ትዕግስት አወቀ እንደገለጹት በተሰጠን ስልጠና ተደስቻለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች በመከፈታቸው ቀደም ሲል የነበረው የስራ ጫና በአንጻራዊነት ሲታይ ተቃሏል ሆኖም ግን የስራው ባህሪ በጣም አድካሚና ለጤና ችግርም ተጋላጭ እያደረገን ስለሆነ ለስራው ክብደትና ለድካማችን የሚመጥን ደረጃና ደምወዝ እንዲሻሻል ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምግብ ቤት ፈረቃ ሺፍት አስተባባሪ ሆነው የሚሰሩት ወ/ሮ አበቡ እውነቴ በበኩላቸው አንድ ወር ከ15 ቀን የፈጀ የምግብ ዝግጅት ስልጠና እንደወሰዱና የሲኦሲ ፈተናም ተፈትነው በማለፋቸው የተደሰቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስልጠናውን በግል ለመሰልጠንና ሲኦሲ ለመፈተን አቅም ስለሌለን በግል ከፍሎ መሰልጠን የማይታሰብ ነበር ያሉት ወ/ሮ አበቡ ዩኒቨርሲቲው ክፍያውን ሁሉ ሸፍኖ ስላሰለጠነን እጅግ በጣም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

ለ32 አመታት ያክል በትጋት ያገለገሉት አንጋፋዋ የወጥ ቤት ባለሙያ ወ/ሮ የሺ ወርቅ ቦጋለ ስልጠናውን የሰጡት መምህራኖች በጣም ጎበዞች ናቸው በተግባር የተደገፈ ስልጠና ነው የተሰጠን ለዚህም ዩኒቨርሲቲያችን እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የግቢ ውበት ላይ እየሰራ ያለው ስራ የሚያኮራ ነው በቀጣይ ግን ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬዎችን መትከል ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ ውበቱም ጥቅሙም ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ በባሕር ዳር ቴክኖሎጅ ተቋም (ፖሊ ግቢ) ለ34 አመታት ያክል በትጋት ያገለገሉት አንጋፋዋ የወጥ ቤት ሽፍት አስተባባሪ ወ/ሮ የካባ ብርሀኑ በዩኒቨርሲቲው ሰርተው፣ ወልደው፣ ከብደው፣ ወግ ማዕረግ ያዩበት በመሆኑ እንደቤታቸው የሚቆጥሩት እና የሚወዱት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ቴክኖሎጅ ተቋም የምግብ ቤት አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ሰናይት ባለው በበኩላቸው ሰራተኞቹ ስልጠና በማግኘታቸው የስራ ተነሳሽነታቸው ጨምሯል ብለዋል፡፡  በስልጠናው የተሳተፉ ሁሉም ሰራተኞች ስልጠና በማግኘታቸው መደሰታቸውን የተናገሩ ሲሆን ሁሉም ሰራተኞች ያነሱት የጋራ ጥያቄ ደረጃና ደምወዛችን ቢሻሻል የሚል ሀሳብ አንስተዋል፡፡