በከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ እየተሰጠ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

የመሬት አስተዳደር ተቋም በከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ እየሰጠ የነበረውን ስልጠና አጠናቀቀ
=============================================
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤትጋር በመተባበር በከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ በተዘጋጁ የሙያ ደረጃዎች ማለትም ከደረጃ II እስከ V ለማሰልጠን እና የሙያ ብቃት ምዘና (COC) ለመመዘን የሚያበቃ ስልጠና ከግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በመሰጠት ላይ የነበረው ስልጠና የማጠቃለያ መርኃ-ግብር በ28/10/14 ዓ.ም በጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ::
ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለመሬት አስተዳደር ተቋም ልዩ ትኩረት እንዳላቸው አውስተው በአገር አቀፍ ደረጃ በሙያው የካበተ ልምድ ያላው የተማረ የሰው ኃይል በብዛት ባለመኖሩ ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ስራ መስራቱንና በትክክል በሙያው ባለቤቶች የተደጋጀ ተቋም መመስረቱን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዘዳንቱ በማስከተል ተቋሙ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ደረጃ ያለና ዩኒቨርሲቲውን በልዩነት ከሚያስጠሩት ፕሮግራሞች አንዱ መሆኑን ገልፀው ተመርቀው የሚወጡት ተማሪዎችም ከሌሎች ሙያዎች በተሻለ መልኩ የስራ እድል እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም መሬት አንዱ የሙስና ዋሻ ስለሆነ የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን ስልጠናው ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ፕሬዘዳንቱ አስገንዝበዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን በበኩላቸው ለሰልጣኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውንና ዩኒቨርሲቲው በግንባር ቀደምትነት ላበረከተው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው ስልጠናው የመሬት አስተዳደር ስርዓቱን ለማዘመን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክብር እንግዳው አክለውም በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የከተሞች መስፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ለህዝቡ አስፈላጊውን የመሰረተ ልማት አውታር በአንድ ጊዜ መዘርጋት አዳጋች መሆኑን አስገንዝበው የከተማ መሬት አስተዳደርን በተለምዶ ከሚሰራበት የአሰራር ስርዓት አላቆ በአዲስ መልክ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በማከናወን የማህበረሰቡን ፍላጎት ያሟላ ስራ እንዲሁም የነበረውን ክፍተት በመሙላት ሰልጣኞች ከስልጠናው መልስ የእውቀት ሽግግር አድርገው ለሌሎች የቀሰሙትን ክህሎት በማካፈል ከታችኛው እርከን ድረስ በመውረድ ስራ እንዲሰሩ በአንክሮ አሳስበዋል፡፡
የሰልጣኞች ተወካይና ከአብክመ የከተሞች ፕላንና ልማት ኢንስቲትዩት የቅየሳ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ወይዛዝርት አሞኘ የስልጠናውን ደካማና ጠንካራ ጎን አሳይተው በርካታ ጠንካራ ጎኖች የታዩ መሆኑንና መሻሻል ያለበት የስልጠናው ጊዜ ማጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመርኃ ግብሩ ላይ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የተውጣጡ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ለሰልጣኞች የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሰልጣኞች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የተውጣጡና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማለትም Cadastral Surveying and Mapping, Cadastral Registry System, Urban Planning and Land Administration እና Real Property Valuation በተሰኙት የሙያ ዘርፎች165 ሰልጣኞች የሰለጠኑ ሲሆን 39 ሴቶች መሆናቸው እንዲሁም በሌሎች አራት ዩኒቨርሲቲዎች፡-ሲቪል ሰርሲስ፣ድሬዳዋ፣አምቦና ወላይታ ሶዶ በተመሳሳይ መልኩ ስልጠናው መሰጠቱ ተገልፆ ለአራቱ የቡድን ተወካዮች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
በማጠቃለያውም ከሙያ ብቃት ምዘና (COC) የስራ ዘርፍ በመጡ ባለሙያዎች ሰልጣኞች ለመመዘን የሚስችላቸውን እውቀት እንዳገኙና የምዘናውን አሰጣጥ ስርዓት የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ ተደርጓል፡፡
በሙሉጎጃም አንዱዓለም