በቴክኖሎጂ የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ነው

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት በዓል በማስመልከት በቴክኖሎጂ የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር (Techno-Business Idea Competition) ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ  እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲዉ 60ኛ ዓመቱን ከመጭዉ መስከረም እስከ ሰኔ 4/2015 ዓ.ም ድረስ በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች እንደሚያከብርና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የ60 ዓመት ጉዞዉን ሊያሳይ በሚችል መልኩ በግብርና፣ በህክምና እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያለዉን እድገት ለመደገፍ እያከናወነ ያለዉን ስራ ለማሳየት ያለመ ነዉ ብለዋል፡፡

በስልጠናዉ የኢንስቲትዩቱ ተማሪዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን በስራ ፈጠራቸዉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድረዉ ከስራ ፈጠራና ክህሎት ሚኒስቴር ዕዉቅናና ሽልማት የተሰጣቸዉ ተማሪዎች ስራቸዉን ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዉ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሜከር ስፔስ አስተባባሪ (BIT maker space coordinater) ወ/ሪት ቤዛወርቅ ጥላሁን እንደገለፁት ፕሮጀክቱ የዩኒቨርሲቲዉ 60ኛ ዓመት ሲከበር መቅረቡ ተቋሙን በሚገባ ከማስተዋወቅ ባለፈ ተማሪዎቹ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ወ/ሪት ቤዛወርቅ አክለዉም ፕሮጀክቱ በአራት ዋናዋና መስኮች ላይ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ የትኩረት መስኮቹም የህክምና ቴክኖሎጂ፣ የግብርና ቴክኖሎጂ፣ የምግብ ማቀነባበርና ተረፈ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ዙሪያ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

ስልጠናዉ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት በገለፃና በመስክ ምልከታ የሚቀጥል መሆኑ መርሀ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ሸጋዉ መስፍን