በሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባኤ

የትምህርት እና ስነ-ባሕሪ ሳይንስ ኮሌጅ ከ BDU-NORHED ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዓለም አቀፍ  ጉባኤ ለሁለተኛ ጊዜ አካሄደ

የትምህርት እና የስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ በኖርዌይ መንግስት በሚደገፈው ከBDU-NORHED ፕሮጀክት  ጋር በመተባበር ሳይንስ እና ሒሳብ  መማር፣ ማስተማር እና  ከተግባር ትምህርት እንዲሁም በንድፈ ሃሳብ ግምገማ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሁለተኛውን አለማቀፍ አውደ-ጥናት የውጭ እና የሀገር ውስጥ ሙሁራን በተገኙበት በዋናው ገቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ታህሳስ 20-21/2015 ዓ.ም በድምቀት ተካሂዷል፡፡

በአውደጥናቱ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ አንጋፋ የትምህርት ባለሙያዎችን የያዘ  ተቋም እንደመሆኑ  በሀገራዊ ጉዳዩች ላይ አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ ኮሌጁ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተሰራው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) እንዲሁም የፖስት ግራጁየት ዲፕሎማ ፕሮግራምን ጨምሮ በለውጥነት የተወሰዱ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሙሁራኑ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ በትምህርቱ መስክ ለሚከሰቱ ችግሮች የመፍትሄው አካል ሆነው እያገለገሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የBDU-NORHED ፕሮጀክት ከትምህርት እና ስነ-ባሕሪ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር  በሀገር አቀፍ ደረጃ አሁን ላይ በሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቀነስ በአውደጥናቱ የሚቀርቡ ጥናቶችን በመቀመር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት እና ስነ-ባሕሪ ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና ተመራማሪ እንዲሁም  የBDU-NORHED ፕሮጀክት አስባባሪ ዶ/ር ዳዊት አስራት በበኩላቸው  ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጀ በሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ ተማሪዎች የሚያስመዘግቡትን  ዝቅተኛ ውጤት  ጨምሮ  የመማር ማስተማር ችግሮችን ለማሻሻል በጉዳዩ ላይ በየዓመቱ አለምአቀፍ አውደ ጥናቶችን በማካሄድ ሙሁራን በጉዳዩ ላይ እንዲመክሩ መድረኮችን በማዘጋጀት በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዳዊት አክለውም ቀጣይ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚሰጡ የሳይንስ እና የሒሳብ ትምህርቶች ላይ ያለውን የትምህርት ሂደት ለማሻሻል ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ ለመስራት በየዓመቱ የሚደረጉ አውደጥናቶች መሰረት እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

በአውደጥናቱ ላይ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያሉ ሙሁራን በሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርት ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ከ20 በላይ የጥናት ወረቀቶች ቀርበው ከታዳሚዎች ጥያቄዎች እና  አስተያየቶች ከመደረክ ምላሽ እና ፅብረቃ ተደርጎባቸዋል፡፡ ለሁለት ተካታታይ ቀናት ቆይታውን ባደረገው አውደጥናት ላይ ጥናታዊ ፁሁፍ ላቀረቡ መምህራን የተሳትፎ የምስክር ወረቀት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እጅ ተቀብለዋል፡፡

በአውደጥናቱ በንግግር የዘጉት  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት  ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው አሁን ላይ  በሳይንስ እና በሂሳብ ትምህርቶች ላይ ያለው ክፍተት ለማጥበብ እየሰራ ያለውን የBDU-NORHED ፕሮጀክትን የቆይታ ጊዜው ሲያበቃ አሁን ያለው የተነሳሽነት ስራዎች  እንዲቀጥሉ ፕሮጀክቶችን ተቋማዊ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ አሁን ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሳይንስ ማስተማሪያ ግብዓቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማምረትና የማሟላት ፣ ከሳይንስ ትምህርቶች ጋር ተያይዞ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ፣ ከዳታ ቤዝ  እና ከጆርናሎች ጋር  ተያይዞ ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎችን በትኩረት መስራት እና በተከታታይ የሳይንስ መምህራንን ማፍራት ስራ ላይ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡