በሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች አውደ ጥናት ተካሄደ

በሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች መማር ማስተማር ላይ ያተኮረ አለማቀፍ አውደ ጥናት ተካሄደ !!
====================================================
በሙሉጌታ ዘለቀ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ ከNORHED PROJECT ጋር በመተባበር በሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች መማር ማስተማር ላይ ያተኮረና የተለያዩ የምርምር ፁሁፎች የቀረቡበት ለሁለት ቀናት የቆየ አለማቀፍዊ አውደጥናት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የNORHED PROJECT ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዳዊት አስራት በአውደጥናቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች ተማሪዎች ያላቸው ፍላጎትና ዝንባሌ መቀነሱን ጠቅሰዋል፡፡ ዶ/ር ዳዊት ቀጥለውም በአውደ ጥናቱም በችግሩ ዙሪያ በታዋቂ ሙሁራን የተሰሩ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ጠቅሰው ይህም በሀገራችን የሳይንስና ሒሳብ ትምህርት ላይ የራሱ የሆነ አውንታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድር እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
 
አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት የሀገራችንን መማር ማስተማርን ለማዘመንና በትምህርቱ ዘርፍ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ በሙያው ውስጥ ያለን ሙሁራን እንደዚህ ያለ አለማቀፍ አውደጥናቶችን በማዘጋጀት አለማቀፍ የሆኑ የተለያዩ የምርምር ፁሁፎች እንዲቀርቡና ክርክር እና ውይይት እንዲደረግባቸው ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
በመድረኩ ላይ ከቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል የእንግሊዝ ሀገሩ የሒሳብ ተመራማሪና ሙሁር የሆኑት ፐሮፌሰር ፓውል ኢርነስት “Mistakes in Mathematics and Learning” በሚል ርእስ እና ኢትዮጵያዊው ሙሁር ዶ/ር ተመቸኝ እንግዳ «Science education: issues and trends” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው በአውደጥናቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች በጥናት አቅራቢዎች ግብረ-መልስ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በሀገራችን የሳይንስና ሒሳብ መማር ማስተማር ስልጠና የሚሰጠው በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርቱን ከመውደድ ይልቅ ትምህርቱን መጥላትና መሸሻቸው በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተፅኖ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ይህንን ቸግር ለመከላከል በሙያው የሰለጠኑ መምህራን ተጨማሪ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ተማሪዎች የሳይንስና የሒሳብ ትምህርቶችን በሚያዝናና እና በጨዋታ መልክ እንዲከታተሉ ቢደረግ በሂደት በመማር ማስተማሩ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ በአውደጥናቱ ላይ ተጠዉሟል፡፡ በአውደጥናቱ ላይ ከሃያ ሰባት በላይ ጥናታዊ ፁሁፍች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
 
በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብይ መንክር ለአውደጥናቱ ተሳታፊዎች የመዝጊያ ንግግርና ለጥናታዊ ፁሁፍ አቅራቢዎች የእውቅና የምስክር ወረቀት በሰጡበት ወቅት እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ይህ አለማቀፍ አውደጥናት ከተለያዩ የአለማትን ክፍሎች ያሉና በሙያው ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ሙሁራን የተሳተፉበት በመሆኑ ለራዕያችን መሳካት መድረኩ ጠቋሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ መድረኮች ችግሮቻችን የሚጠቁሙና መፍትሄም የሚያፈልቁ በመሆኑና ዩኒቨርሲቲያችንም ከፍተኛ ልምዶችን የሚያገኝበት በመሆኑ የሚበረታታ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
 
በምክክር መድረኩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የውጭ ሀገር ሙሁራን፣ የትምህርት ቢሮ ሀላፊዎችና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡