በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ ምክክር ተካሄደ

በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሄደ

**************************************************

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የሁሉም ግቢዎች የፀጥታና ደህንነት  ባለሙያዎች፣  የተማሪዎች ህብረት አመራሮችና ከሌሎች አደረጃጀቶች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት  በተገኙበት  በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ በጥበብ  ህንፃ  የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተካሄደ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ገደፋዉ ሽፈራዉ  እንደገለፁት በሀገራዊ ጉዳዮች እና በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ ችግሮች ከመፈጠራቸዉ በፊት ተቀራርቦ መነጋገር ሊፈጠር የሚችልን ችግር ለማስወገድ ቁልፍ መፍትሄ ነዉ ብለዋል፡፡ አቶ ገደፋዉ አክለዉም አገልግሎት ሰጭ አካላት ለተማሪዎች ተገቢዉን አገልግሎት በመስጠት ለችግር መንስኤ የሆኑ ነገሮችን መቅረፍ ይገባል ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን ዶ/ር ምኒችል ግታው በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶች በጊዜዉ የእርምት እርምጃ ካልተወሰደባቸዉ ወደ ሌሎቹ ተቋማት የመስፋፋት እድላቸዉ ሰፊ ነው፡፡ ችግሮች ሳይፈጠሩ ቀድመን መከላከልና ማረም አለብን፤ ስለዚህ መብሰል፣ ማስተዋልና ሰከን ማለት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ የፀጥታና ደህንነት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር ሀብታሙ መለሰ በበኩላቸዉ እንደሀገር የፀጥታ ሰጋቶች መኖራቸዉን ገልፀዉ የትምህርት ተቋማት መጥፎም ሆነ በጎ ተግባር የሚፈበረክባቸዉ ስለሆኑ መጥፎውን በማስወገድ በጎ ተግባራት እንዲበራከቱ መስራት ከቻልን የሀገራችንን ሰላም ለመመለስ ሚናችን ከፍተኛ ነዉ ብለዋል፡፡ የአደረጃጀቶች ዓላማ ሰላማዊ መማር ማስተማር እዲኖር ማድረግ በመሆኑ ቅንጂታዊ አሰራራችን በማጠናከር ስጋቶችን ማስወገድ አለብን ብለዋል ኢንስፔክተር ሀብታሙ፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የተለያዩ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን ከዚህ ቀደም ዉይይቶች የሚካሄዱት ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ እንደነበር ገልፀዉ ስጋቶችን መነሻ በማድረግ ቀድመን መወያየታችን ይበል የሚያስብል ነዉ ብለዋል፡፡ ተሳታፊዎች አክለዉም ችግሮችን በመፍታት ሰላማዊ መማር ማስተማሩን ማስቀጠል ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

    ዘጋቢ፡- ሸጋው መስፍን