በሀገራዊ የምክክር ሂደት እና አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ የውይይት

በሀገራዊ የምክክር ሂደት እና አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሄደ

*****************************************************************

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ልታካሂደው ላቀደችው አገራዊ ምክክር መድረክ ግንዛቤ የፈጠረ ምሁራዊ የምክክር ጉባኤ "በሐገራዊ  ምክክር  ሂደት  የባለድርሻ አካላት  ሚናና  ኃላፊነት" በሚል መሪ ቃል የካቲት 22/2014 ዓ.ም በጥበብ ህንጻ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመንግስትና የግል የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

 የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ  አሁን ላይ ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የእኛ እና የነሱ ፖለቲካ  ውሉ የጠፋበት ድሮ የማናውቀው ህይወት የሚከፈልበት፣ሕዝብ የሚሰቃይበት እና የሀገር ሀብት የሚወድምበት  እንደሀገር ችግር ውስጥ የገባንበት እንቆቅልሽ ውስጥ ስለሆንን ችግሩን ለመፍታት ዕውቀት ፣ጥበብና በጥልቀት ማሰብን እንደሚጠይቅ ተናግረው አገራዊ ምክክር መድረክ እንዲሳካ ከምሁራን ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

በምሁራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ በቅርቡ የተቋቋመውን አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስመልክቶ ሦስት ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበዋል፡፡ የሰላም እና የግጭት ተንታኝ፣ የግጭት አፈታት ባለሙያ፣ በማንነት ላይ የተመሰረተ የግጭት ተመራማሪ፣ አቶ ድጋፌ ደባልቄ “ Large Group identity: Moving in and out of “ Glory” and Trauma” በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋኩልቲ መምህር፣ ዶ/ር አደም ካሴ “ብሔራዊ ውይይት ለምን፣ ለማን እና እንዴት፡ አንፃራዊ እሳቤዎችና ግንዛቤዎች”  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕ/ር ወርቁ ያዜ “በሀገራዊ የፖለቲካ ምክክር ሂደት የአማራ ተሳትፎ፡- የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች ሚና እና ኃላፊነት” በሚሉ ርዕሶች የመወያያ ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረቡት ጥናታዊ ወረቀቶችን ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን በማንሳት ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ስናይ  የውስጥን ችግር  ምክንያት በማድረግ ምዕራባዊያን  ሀገራት ለራሳቸው የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የተለያዩ ደባዎችን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን የጠላቶቻችን አካሄድና ሁኔታ በመገንዘብ እንደ ሀገር ሕዝባዊ አንድነትን በማጠናከር ሀገራችንን ከመፍረስ ልንታደጋት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በማንነቱ የተነሳ መፈናቀልን፣ መገደልን፣ መሳደድን በተደጋጋሚ እያስተናገደ በስጋት እንዲኖር የተደረገው የአማራ ህዝብን የማያግባባ የህገ-መንግስቱ ጉዳይ ብዙ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ እና የሀገራዊ ምክክሩ ቢዘገይም ሀገር ነውና መደረጉ ተገቢ መሆኑን ዶ/ር እሰይ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና  ማሕበረሰብ  እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የ2ኛ ዲግሪና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡