ስፖርታዊ ውድድር በሰባታሚት ማረሚያ ቤት

የሰባታሚት ማረሚያ ቤት ስፖርታዊ ውድድሮችን ማካሄድ ጀመረ

*******************************************************

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከባሕርዳር ከተማ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጋር በመተባበር በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች ሰባታሚት በሚገኘው የማረሚያ ቤቱ ስፖርት ሜዳ ከሚያዚያ 7/2014 ዓ.ም ጀምሮ ስፖርታዊ ውድድር ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ የስፖርት ሳይንስ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዘመኑ ተሾመ ፕሮግራሙን ሲከፍቱ እንደገለጹት ውድድር ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያት ታራሚዎች በቆይታቸው ከብቸኝነትና ተስፋ ከመቁረጥ ስሜት እንዲወጡ ለማድረግና አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤናቸው ተጠብቆ የፍረድ ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ መልካም እና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

የአብክመ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የህግ ታራሚዎች ማረምና ማነጽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያዜ መኮነን በበኩላቸው ውድድሩ ለስነ ልቦና፣ ለአካል እና ለጤና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉ በተጨማሪ በታራሚዎች እና በማረሚያ ቤቱ አባላት መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል፡፡ ውድድሩ ለአንድ ወር ከ15 ቀን እንደሚቆይም ገልፀዋል፡፡

ስፖርታዊ ውድድሩ የተካሄደው በታራሚዎችና በጥበቃ ሰራተኞች (ወታደሮች) መካከል ሲሆን በውድድሩ ላይ የተካሄዱት የስፖርት አይነቶችም መረብ ኳስ፣ ገመድ ጉተታ እና እግር ኳስ ናቸው፡፡

በመጨረሻም የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅ ከሆኑት መካከል የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ ዳንኤል ጌትነት የፕሮግራሙን መጀመር ታራሚዎች በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበር በመግለፅ ቀጣይነት እንዲኖረውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ሌላው የማህበረሰብ ክፍል ለስፖርታዊ ውድድሩ አስፈላጊ የሆኑ የቁሳቁስ ድጋፎችን ቢያደርግልን የሚል መልክት አስተላልፈዋል፡፡ 

ዘጋቢ፡- ባንቹ ታረቀኝ