ስራ ፈጠራ እና ንግድን ማዕከል ያደረገ አውደ ጥናት

ስራ ፈጠራ እና ንግድን ማዕከል ያደረገ አውደ ጥናት ተካሄደ

************************************************

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ  ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ከባሕርዳር እስከ ደብረ ማርቆስ ድረስ ባለው መንገድ መዳረሻ ላይ በስራ ፈጣሪዎች ስነ-ምህዳር ካርታ ክፍተት ትንተና እና ንግድን ማዕከል ያደረገ አውደ ጥናት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቡሬ ከተማ ተካሄደ፡፡

መርሃ-ግብሩን በንግግር የከፈቱት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ እንደገለጹት በየአመቱ ከዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ወጣቶች ስራ አጥ እየሆኑ ነው፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ዓላማም ወጣቶች ስራ ፈጥረው ራሳቸውን እንዲመሩ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃና የስራ አፈጻጸም ያቀረቡት የፕሮጀክቱ ኃላፊ ዶ/ር ጌታሁን የማታ ሲሆኑ የፕሮጀክቱ ዓላማ ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት የስራ አጥነትን ችግር መቅረፍ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲኖረውም በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙት ማዕከላት በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

ዶ/ር ጌታሁን አክለዉም ከባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ እና ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁና በመማር ላይ ያሉ የስራ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸው በርካታ ወጣቶች አሉ ይህን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ማስፋፋት ይገባል ብለዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የስራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ላቀ በበኩላቸዉ ከባሕርዳር እስከ ደብረ ማርቆስ ድረስ ባለው መንገድ መዳረሻ ላይ በስራ ፈጣሪዎች ስነ-ምህዳር ካርታ ክፍተት ትንተና እና ንግድ ማዕከል ያለውን መዳረሻና በስራ ፈጠራና ንግድ ዘርፍ ለመሰማራት ያለውን ውጣውረድ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

አቶ ዘውዱ ላቀ የአሰሪና ሰራተኛ ቁጥር ባለመመጣጠኑ በየአመቱ የስራ አጥ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የስራ አጥነትን ችግር መፍታት ለሀገራችን ወሳኝ ነው፡፡ በአለም ላይ ያደጉ ሀገሮችን ስንመለከት ስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርገው በመስራታቸው ማደግ ችለዋል፡፡ እኛም ከመማር ማስተማር በተጨማሪ የክልሉ ወጣቶች ስራ እንዲፈጥሩ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል አቶ ዘውዱ ላቀ ፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጅ ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ታረቀኝ እንደገለጹት የንግድ ማበልጸጊያ ማዕከላት በስፋት ሊቋቋሙ ይገባል፡፡ ስራ ፈጥረው ንግድ ከሚጀምሩት መካከል ተግዳሮት ስለሚበዛባቸው ዘጠና በመቶው በአጭር ጊዜ ይዘጋሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ስራ ተገቢውን ትኩረት ሊያገኝ ይገባል ብለዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የWA ዘይት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ እዮብ ወረታው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲዎች ከቲዎሪ ባለፈ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ሊሰጡ ይገባል፡፡ ለዚህም የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስርን በማጠናከር ተማሪዎች የተግባር ልምምድ በፋብሪካዎች በማድረግ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል አቶ እዮብ፡፡

የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን ከፕሮጀክቱ ሀላፊዎችና አስተባባሪዎችም ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር  ዩኒቨርስቲ  የምርምርና  ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት የንግድ ውድድር ባህል ቀጣይነት እንዲኖረው ቢደረግ በአገራችን ትልልቅ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች እውቀታቸውን አፍልቀው ለባለሀብቱ እየሸጡ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ባገኙት ገቢም እራሳቸውንና ሀገርን ይለውጣሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስርን በማጠናከር ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት በተግባር ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ልምምድ በማድረግ ነው የአደጉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም በየጓዳው ያሉ ጸጋዎችን አውጥተን እና አሳድገን የማህበረሰባችን ህይወት ማሻሻልና መለወጥ አለብን ብለዋል፡፡ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፤የግል ባለሀብቶች፤ የሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ማዕከላት ጥሩ ልምዶችን እና ተሞክሮዎችን  በማጎልበት ሊሰሩ እንደሚገባ ዶ/ር ተስፋዬ አሳስበዋል፡፡

የስምምነት ሰነድ ረቂቅ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከውይይቱ የተገኙ ግብአቶች ተካተውበት በቀጣይ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነትና ሚናቸውን ለይተው መስራት እንዲችሉ ይፈራረማሉ ተብሏል፡፡

በአውደ ጥናቱ የልማት ባንክ ተወካይ፤የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን፤የባሕርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፤ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፤ ከWA ዘይት ፋብሪካ፤ከባሕርዳር ከተማ አስተዳደር፤ ከምስራቅና ምእራብ ጎጃም ዞንና ወረዳዎች የስራ ፈጠራና ክህሎት ቢሮዎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡