የመሬት ጉባኤ ተካሄደ የመሬት ጉባኤ

6ኛው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የመሬት ጉባኤ ተካሄደ
******************************
ግንቦት 25/2015 ዓ/ም፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ] የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም ከኢትዮጵያ መሬት አሥተዳደር የባለሙያዎች ማኅበር ጋር በመተባበር "የኢ-ላንድ አስተዳደርን ለመልካም አስተዳደርና ለዘላቂ ልማት ማስተዋወቅ“ በሚል መሪ ቃል 6ኛው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የመሬት አውደጥናት የአማራ ክልል የመሬት ቢሮ ሃላፊ ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ምሁራን በተገኙበት በባሕር ዳር ከተማ ዩኒሰን ሆቴል ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው መክፍቻ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም ዲን ዶ/ር በላቸው ይርሳው እንዳሉት በመሬት አስተዳደር ዙሪያ ፖሊሲዎችን ለማውጣት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር ፤ በቴክኖሎጂ ታግዞ በአግባቡ የተጠናከረ መረጃ ለማስቀመጥና ብሎም የሀገሪቱን የመሬት አያያዝ፣ አጠቃቀም እና አሥተዳደር ለማዘመን አስተዋፆው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመሬት አያያዝና አጠቃቀምን ለማዘመን ኢንስቲትዩቱ በየዓመቱ ተማሪዎችን ከማብቃት በተጨማሪ ለተለያዩ ባለሙያዎች አጫጭር ሥልጠናዎችን አዘጋጅቶ መስጠቱን እና በሀገሪቱ ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትም ከሚመለከታቸው የመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአውደጥናቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የባሕረ ዳር ከተማ የጣና ፎረም የምክክር መድረክን ጨምሮ በርካታ ሀገርአቀፍ እና ዓለምአቀፍ ጉባኤዎችን የምታስተናግድ መሆኗን ጠቅሰው ለግዙፉ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መነሻው የቀድሞው የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት እና የባሕር ዳር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከምስረታው ጀምሮ እሰካሁን ባለው በመማር ማስተማር በምርምሩ ዘርፍ ካበቃቸው ሙሁራን በተጨማሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት ፕሮግራሞች በየጊዜው በማሳደግ በአሁኑ ሰዓት ከ429 በላይ ፕሮግራሞች ፣ በስድስት ፕሮግራሞች የልዕቀት ማዕከል፣ ከ232 በላይ አጋር ተቋማት ያሉት እና በጠንካራ አመራር እና ልምዱ ቀዳሚ እና ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከታጩ ቀዳሚ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አነዱ ሆኖ መመረጡን ዶ/ር ፍሬው ተናግረዋል፡፡
በአውደጥናቱ መክፈቻ ላይ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም በሚሰራቸው የምርምር ስራዎች እና በየዓመቱ እያስመረቀ በሚያወጣቸው ባለሙያዎች አማካኝነት የክልሉ የመሬት አስተዳደር ስረዓት በእጅጉ እየዘመነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ በየዓመቱ መሬትን አስመልክቶ በሚያካሂደው አውደጥናት ላይ የሚቀርቡ የምርምር ውጤቶችን የክልሉ መንግስት የእቅዱ አካል በማድረግ በሁሉም ዞኖች ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት 18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር የተበጣጠሰ የገጠር መሬት በ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን አባውራዎች ይዞታ ሥር ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በተሠራው ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ሥራ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባወራዎች ይዞታ ስር የሚገኝ ከ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተበጣጠሰ መሬት የማረጋገጫ ደብተር እየተሰራላቸው መሆኑን አቶ ሲሳይ ዳምጤ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይን ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የስራ ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል ላሬቦ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠር እና የከተማ መሬት በአግባቡ ከዘራፊዎች እጅ በማውጣት የህዝብ ተጠቃሚነትን እና ዘላቂ የልማት አቅጣጫዎች እንዲቀመጡ ከማድረግ አኳያ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም በየዓመቱ የሚያካሂዳቸው አውደጥናቶች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች ከሚባሉት ውስጥ የመሬት አስተዳደር ጉዳይ አንዱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያም ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዎች የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር በመፍጠር ከተቋማቶች ጋር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በመሬት አጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የኢ-ላንድ አስተዳደርን ለመልካም አስተዳደርና ለዘላቂ ልማት ማስተዋወቅን አስመልክቶ ለጉበኤ ታደሚዎች ቁልፍ ንግግር አድርገዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም አዘጋጅነት "የኢ-ላንድ አስተዳደርን ለመልካም አስተዳደርና ለዘላቂ ልማት ማስተዋወቅ" በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ላይ የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም፣ የመሬት መረጃ አያያዝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን እና ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ እና የመሬት አስተዳደር ፓሊሲና ሕግን በተመለከተ 13 የጥናት ወረቀቶች ቀርበው የጉባኤው ተሳታፊ ሰፊ ክርክርና ውይይት አድርገዋል፡፡
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ከተለያዩ ተቋማት በመምጣት በአውደጥናቱ ላይ ጥናታዊ ወረቀት ያቀረቡ እና ለአውደጥናቱ መሳካታ የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ giz እና USAID እና የኢትዮጵያ መሬት አሥተዳደር የባለሙያዎች ማኅበር በዩኒቨርሲቲው የምርመር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ከዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እጅ የእውቅና ሰረትፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡