የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የባህል ትውውቅ መድረክ

ኢትዮጵያ በዩኒስኮ ካስመዘገበቻቸው ዘጠኝ ቅርሶች መካከል ሶስቱ በአማራ ክልል እንደሚገኙ ተገለፀ

የሰላም ሚኒስቴር ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚያሰለጥናቸው የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የባህል ትውውቅ መድረክ በስራ አመራር አካዳሚ አዳራሽ በድምቀት ተካሂዷል፡፡

በትውውቅ መድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አየለ አናውጤ ለመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለፁት አማራ ክልል በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን የያዘ፤ ከ20 በላይ ዞኖችና ሪጂኦ ፖሊታን ከተሞች የተዋቀረ፤ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶችን የያዘ ክልል ነው ብለዋል፡፡ክልሉ ስያሜው የአማራ ክልል ይሁን እንጂ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን አቅፎ የያዘ ክልል ነው የሚሉት ዶ/ር አየለ ለበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች እውቅና በመስጠት የመንግስታዊ መዋቅሩ አካል ያደረገ ክልል ነው ብለዋል፡፡ለዚህም ለኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን፣ ለአዊ ብሄረሰብ ዞን፣ ለዋገኸምራ ብሄረሰብ ዞን እና ለአርጎባ ልዩ ወረዳ  ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ እድል የሰጠ ብቸኛው ክልል ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ህዝብ ለመንግስት ስርዓት እውቅና የሚሰጥ ህዝብ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር አየለ ችግሮች በመንግስት ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ይፈታሉ ብሎ የሚያምን ህዝብ ነው ብለዋል፡፡አክለውም በክልሉ በርካታ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች መኖራቸውን የጠቀሱ ሲሆን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግስታት እና የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ሀገራችን በዩኒስኮ ካስመዘገበቻቸው ዘጠኝ ቅርሶች መካከል ሶስቱ ናቸው ብለዋል፡፡በቅርቡ ደግሞ ጣና እና በጣና ውስጥ ያሉ ገዳማት በዩኒስኮ ለመመዝገብ ጫፍ ላይ ደርሰዋል በማለት የአሁኑ ትውልድም አዲስ ታሪክ የሚሰራ፣ የራሱን ታሪክ ፅፎ የሚያልፍ፣ ለችግሮች የማይበገር መሆን አለበት ሲሉ ወጣቶችን መክረዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር የሻምበል አጉማስ “ የወጣትነት የለውጥ አብርሆት ” [መፈተኛ ቤተ ሙከራ] በሚል ርዕስ ለታዳሚዎች ቁልፍ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ የለውጥ አብርሆት መነሻ፣ መጓዣ መንገድ እና መዳረሻ አለው የሚሉት ዶ/ር የሻምበል መነሻው ለውጥ ለምን አስፈለገ? የሚል ሲሆን አሁን እንደ ሀገር የገጠመን የሀገር መፍረስ፣የስራ አጥነት፣የስንፍና … አደጋ  የለውጥ አብርሆት መነሻ ነው፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ መጓዣ መንገዱ ደግሞ እውነት ላይ መቆም፣ በእውቀት መመላለስ እና በጥበብ ማትረፍ ናቸው ይላሉ፡፡የለውጥ አብርሆት መዳረሻዎችን ሲገልፁ ደግሞ ሰብዓዊ መሆን፣ መክሊታዊ መሆን እና ሳይንሳዊ መሆን ናቸው በማለት ለወጣቶቹ ሳይናሳዊ ትንታኔዎችን ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ከተለያዩ  ብሄር ብሄረሰቦች የመጡ ወጣቶች የየአካባቢያቸውን ባህላዊ ጭፈራዎች ያቀረቡ ሲሆን አዝናኝና አስተማሪ ጭውውት፣ ግጥሞች፣ ፉከራና ሽለላዎች ቀርበው የመድረኩን ተሳታፊዎች ሲያዝናኑ አምሽተዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማው አሸብር ፕሮግራሙ በተሳካ መንገድ እንዲካሄድ አስተዋፅኦ ለነበራቸው ተባባሪ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡አቶ ግርማው አክለውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት መሰል ፕሮግራሞችን በማዘጋጀትና በማስተባበር እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከሰላም ሚኒስቴር ተወክለው ስልጠናውን እያስተባበሩ የሚገኙት አቶ አለማየሁ ለማ የመዝጊያ ንግግር ያቀረቡ ሲሆን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ስልጠናው ተጀምሮ እስኪያልቅ ኮሚቴ በማዋቀር ላደረጉት ድጋፍ እንዲሁም ለክልሉና ለከተማ አስተዳደሩ የፀጥታና ደህንነት አካላት ሰልጣኞች ያለምንም የፀጥታ ስጋት ስልጠናቸውን እንዲከታተሉ በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዕለቱ የባህል የትውውቅ መድረክ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ህዝብ መዝሙር በጋራ በመዘመር ተጠናቋል፡፡