ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኞች

ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኞች ከተመዋን ማፅዳት ጀመሩ

ህዳር 4/2015 ዓ/ም (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) 

በሰላም ሚኒስቴር እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትብብር ‹‹በጎነት ለአብሮነት›› በሚል መሪ ሃሳብ ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ ከ2000 በላይ ወጣቶች ለ33 ቀናት የሚቆይ ስልጠና  በባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ሲሆን በዛሬው እለት ከዋናው  ፔዳ  ግቢ እስከ  ዊዝደም  አደባባይ  የሚገኘውን  መንገድ ከበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ጋር በመቀናጀት የመጀመሪያ የሆነውን  ብሔራዊ  የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ጀምረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ዘውዴ ኤጄርማ በጎ ፈቃድ ሰጭዎቹ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ በመደበኛ ስልጠና የወሰዱትን ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ዛሬ የበጎ ፈቃድ ስራን በፅዳት ጀምረዋል፡፡ ወጣቶቹ በአገሪቱ ከሚገኙ ሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ሲሆኑ ስልጠናውን ለ33  ቀናት  ከወሰዱ በኋላ ከሚኖሩበት አካባቢ ራቅ ወዳለ ቦታ ተመድበው ለ10 ወር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  እንዲሰጡ  ይደረጋል፡፡  የዛሬው  የፅዳት  ስራም  ለቀጣይ ስራዎች  መነሳሳትን  ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡

አቶ ዘውዴ ስለዓላማው ሲናገሩ ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር፣ አካባቢውን  ማፅዳትና አቅመ ደካሞችን መርዳት፤ በጎነትን ማነሳሳት እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሸረሸረ የመጣውን አንድነት ማጠናከር ነው ብለዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጊዜው ታከለ  በበኩላቸው ከሰላም ሚኒስቴር የመጡ የበጎ ፈቃድ የሚሰጡ  ወጣቶች ዛሬ  የፅዳት ስራ  የጀመሩባት  ከተማ በተፈጥሮ የታደለች፣ ብዙ ታሪካዊ ቦታዎች በሚገኙበት፣ የአማራ ባህልና እሴት  የሚንፀባረቅባት  ባሕር  ዳር ከተማ ናት፡፡  በተፈጥሮ ውብ ከመሆኗ  ባሻገር ነዋሪዎቿ  በየጊዜው  አካባቢያቸውን በማፅዳት፤ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ  ለኑሮ እና ለቱሪስት  ምቹ እንዲሆን እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን ዛሬም ይህን ለማስቀጠል ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር  እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን ለመስጠት ከደብረ ማርቆስ ከተማ የመጣው ወጣት ወንዳለ ይሄነው  እንደተናገረው በሳምንቱ የስልጠና ቆይታችን ስለ ህይወት ያለንን አስተሳሰብ፤ ትናንትናችን በደንብእንድናይ፣ ዛሬአችን ደግሞ በደንብ እንድናመዛዝን አድርጎልናል፡፡ ከዚህ በኋላም ከምንሄድበት  ማህበረሰብ ጋር እንዴት መቆየት እንዳለብን ጥሩ ስንቅ ሆኖናል፡፡ የዛሬውም የበጎ ፍቃድ  አገልግሎት እንደመጀመሪያ ስልጠናውን በተግባር ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ ለበጎ ፈቃድ ሰልጣኞች መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲአጠቃላይ ጥራት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አንዳርጋቸው ሞገስ በጎ ፈቃድ ሰጭዎቹ በቀጣይ ፕሮግራም የተያዘውን ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ማለትም እንቦጭን ማፅዳት  እና የደም መለገስ ተግባራት ላይ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡