iuc

BDU-IUC ፕሮጀክት ከግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የክረምት ችግኝ ተከላ አካሄደ

22 Jul, 2026

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ሀምሌ 09/2018 ዓ.ም.

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ BDU-IUC ፕሮጀክት ከግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር፣ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ አካል የሆነውን የክረምት ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ዘንዘልማ ቀበሌ፣ ደወል ጎጥ ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው የቦረቦር ልማትና ማዳን ስፍራ አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ የBDU-IUC ፕሮጀክት ማናጀር ተስፋዬ ሽፈራው(ዶ/ር)፣ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ሰራተኞችና ተማሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ በንቃት ተሳትፈዋል። በዚህም ለአካባቢው ተስማሚና የቦረቦር መስፋፋትን በመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የተመረጡ የአገር በቀልና ሌሎች የዛፍ ችግኞች ተተክለዋል።

የመርሃ ግብሩ አስተባባሪና የBDU-IUC ፕሮጀክት የእፅዋት ቤተ መዘክር ኃላፊ አቶ ጌታሰው ሞገስ እንደገለጹት፣ የችግኝ ተከላው በበጋ ወቅት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን፣ በተለይም ከእንጨትና ከድንጋይ የተሰሩ የጎርፍ መከላከያ እርከኖችን (Wooden with Stone Check Dams) ለማጠናከር እና መሬቱ በተፈጥሮ እንዲያገግም በማሰብ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የተጎዱ መሬቶችን መልሶ ማገገም፣ የአፈር መራቆትንና የቦረቦር መስፋፋትን መቆጣጠር፣ ለምርምርና ለትምህርት የሚያገለግል ሰርቶ ማሳያ ማቋቋም፣ እንዲሁም ማህበረሰቡን በቀጥታ በማሳተፍ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር ዋና ዓላማው መሆኑ ተገልጿል።

በመጨረሻም፣ BDU-IUC ፕሮጀክት በምርምር፣ በትምህርትና በማህበረሰብ አገልግሎት የሚገኘውን ዕውቀት በተግባር በማዋል፣ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራዎችን በቀጣይነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ሆኖ እንደሚሰራ ተገልጿል።

iuciuc