“ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ መሆን የሚያስችለውን የተሟላ ዝግጅት አድርጓል።”
27 Nov, 2025
“ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ መሆን የሚያስችለውን የተሟላ ዝግጅት አድርጓል።” ዶ/ር መንገሻ አየነ። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ (ህዳር 18/2018 ዓ/ም)፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ መሆን የሚያስችለውን የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ገለጹ፡፡ ዶ/ር መንገሻ አየነ በህዳር 16/2018 ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በአደረጉት ቆይታ “ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ መሆን የሚያስችለውን የተሟላ ዝግጅት አድርጓል። ይህ ዝግጅት በምርምር፣ በመማር ማስተማር፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በማህበረሰብ አገልግሎት ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ለመዝለቅ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተሻለ አካዳሚያዊ፣ የፋይናንስና አስተዳደር ነፃነት ኖሯቸው ለትምህርት ጥራት እንዲሰሩ ራስ ገዝ መሆናቸው መልካም ጅማሮ መሆኑ እንደተመከረበት አስታውሰው ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አሥሩ ራስ ገዝ እንዲሆኑ የማድረግ ጥረት የቀጠለ እንደሆነና ከእነዚህ መካከል ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሆኖ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የሀገሪቱ አቅምና ገበያውን መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል ለማፍራት የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት ወሳኝ መሆኑን አንስተው ለዚህም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይል ስምሪት፣ ሃብት የማመንጨት አቅም፣ አስተዳደራዊ መዋቅርና መሰል ተግባራትን በማካተት ውስጣዊ ግምገማ በማድረግ ውጤቱን ለትምህርት ሚኒስቴር መላኩን ገልፀው፣ የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር በሚሰጠው ፈቃድ መሰረት የዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝነት አሰራሩን ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ !