በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የፓናል ዉይይት ተካሄደ

የፖለቲካል ሳይንስና አለማቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ያሉ ብሔር ተኮር ጥቃቶች፤ ግጭቶች፤መፈናቀሎች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች( Ethnic based attacks, conflicts and displacement in Ethiopia since 2018, the Way out) በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፖናል ዉይይት አካሄደ፡፡ የፓናል ዉይይቱ የተካሄደዉ በቀን 19/06/2013ዓ.ም በቀድሞዉ ሴኔት አዳራሽ (Old Senate hall) ሲሆን የውይይቱ ጥቅል መረጃ እንደሚከተለው ነው፡፡

መግቢያ

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፤ ማህበራዊ ሳይንስ ፋካልቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለማቀፍ ጥናት ት/ክፍል በአገራዊና አሁናዊ ሁኔታዎች ላይ ምሁራዊና የሃሳብ መድረኮችን ማዘጋጀት አላማ ያደረገ ተከታታይነት ያላቸው የፓናል ውይይት መድረኮች እያዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል፡ የዛሬው ፓናል ውይይትም የዚህ ተከታታይ ውይይት አካል ሲሆነ በመሰረታዊነት ትኩረቱ ብሄር ተኮር ጥቃቶች፤ግጭቶችና መፈናቀል በኢትዮጲያ እና መውጫ መንገዶች (መፍትሄዎች) ላይ ያኮረ ነው፡፡

ለዚህ የፓናል ውይይት ሶስት ምሁራንና ባለሙያዎች የተለያዩ የጥናት ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን በቀረቡት ጥናቶችና ምልከታዎች ላይም ሰፊ ውይይትና የሃሳብ ክርክሮች ተደርገዋል፡፡

ውይይቱን በማስተዋወቅ የጀመሩት የማህበራዊ ሰይንስ ፋካልቲ ዲን ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ ናቸው፡ በንግግራቸው የውይይቱን ታዳሚዎችና ጥናት አቅራቢዎች በማመስገንና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእታቸውን በማስተላለፍ የጀመሩ ሲሆን ይሄ ውይይት በኢትዮጲያ ፖለቲካ ሽግግር ላይ የሚደረጉ ተከታታይነት ያላቸው የውይይት መድረኮች አካል እንደሆነና ተመሳሳይ መድረኮች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸወውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የፓናሉ ጠቅላላ ሂደት ና ፓናሊስቶቹን ካስተዋወቁ በኋላ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ Project Development and Management Director የሆኑትን ዶ/ር ጌታሁን የማታን ጋብዘዋል፡፡

ዶ/ር ጌታሁን የማታ ፡ ለተሳታፊዎችና ጥናት አቅራቢዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በማስተላለፍ፡ የማህበራዊ ሳይንስ ፋልክቲ በዋናነት ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስና አለማቀፍ ጥናት ት/ክፍል በተለያዩ ዘርፎች እያደረጉት ላለው እንቅስቃሴ አድናቆታቸውን ገልጽዋል፡፡ የዛሬው የፓናል ውይይጥ ሃሳብም ወቅቱን የጠበቀና መሬት ላይ ያለን ጉዳይ ለውይይጥ ማቅረቡ በጉዳዩ ላይ የሰዎችን ግንዛቤ የሚጨምር ለሚመለከተው አካም የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ፋካልቲውንና የትምህርት ክፍሉን በማመስገን ውይይቱ መከፈቱን አብስረዋል፡፡

የውይይቱ ሂደት

የፓናል ውይይቱ ሶስት ምሁራን ባቀረቧቸው ጥናቶችና ሃሳቦች ላይ ያጠነጠነ ሲሆን፡ ዶር ሲሳይ መንግስቴ (በአዲስ አበባ ዩኑቨርሲቴ የፌደራሊዝም ጥናት መምህርና ተመራማሪ) Ethnic-based attacks and conflicts in Ethiopia: Cause And Effects በሚል ርዕስ፡ አቶ ታደሰ መለሰ (በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር) Metekel: Post 2018’s Political Change and the Conflict Dynamics በሚል ርዕስ፡ አቶ ምግባሩ አያሌው (ሰላም ሚኒስትር ባልደረባ) Conflicts in Ethiopia since the reform and the way outs በሚል ርዕስ የጥናት ውጤቶቻቸውንና ምልከታዎቻቸውን አጋርተዋል፡፡

ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ፡Ethnic-based attacks and conflicts in Ethiopia: Cause and Effects ብሄር ተኮር ግጭቶችን እና እነዛን ተከትለው የሚመጡ መፈናቀሎችን ለማወቅ የአገራችንን የብሄር ፖለቲካ ታሪክ ቢያንስ ውደ ኋላ 50 አመታትን ሄዶ ማየት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፡ በዚህም የ1960ቹን የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ሲቀነቀኑ የነበሩ ጥያቆዎች በመዘርዘር፡ ከነዚህ ጥያቄዎች በኋላ ላይ ጎልቶ የወጣው የብሄሮች ጥያቄ አንዱ መሆኑን አስረደተዋል፡ የብሄሮች ጥያቄም የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትን መውለዱን ይሄ ደግሞ አሁን ለምናያቸው የብሄር ተኮር ግጭቶች መነሻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የብሄር ተኮር ግጭቶች መነሻ ምክንያት ስልጣን፡ መሬትና የተፈጥሮ ሃብትን ለብቻ የመቆጣጠር ፍላጎት እንደሆነ በመግለፅ በ20ኛው ክ/ዘ አለም ያስተናገደቻቸውነ የባልካን፡ የሩዋንዳ፤የቺቺንያና ሩሲያ ጦርነቶች፡ የህንድ፤ የዳርፉር ወዘተ ግጭቶችን እንደ ምሳሌ ዘርዝረዋል፡፡

የብሄር ተኮር ግጭቶች በኢትዮጲያ ባለፉት 30 አመታት የተጀመረ ሲሆን በባሰ መልኩ የታየው ሃገራዊ ፖለቲካዎ ለውጡን ተከትሎ ባፉት 3 አመታት ነው፡ ይሄም በኦሮሞና በሶማሌ፡ በጉጂ ኦሮሞና በጌዴዮ፤ ወለጋና ሆሮ ጉድሩ በአማሮች ላይ፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በአማራና አገው ላይ፡ እንዲሁም በቅርቡ የህግ ማስከበር ሂደት ወስጥ ማይካድራና ራያ ላይ ማሳያ ናቸው ያሏቸውን ብሄር ተኮር ጥቃቶችን ዘርዘረዋል፡፡

ብሄር ተኮር ግጭቶችን ህጋዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው የፌደራል አወቃቀሩ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ገልፀው፡ በተለይ የአማራው ህዝብ ለደረሰበት መከራና ከጥንተ ግዛቶቹ ለተወሰዱበት ቦታዎች የአማራው ተወካዩች ያሳዩት ዝምታ ዋጋ አስፈከፍሏል ብለዋል፡፡

ብሄር ተኮር ግጭቶችና ችግሮች አሳሳቢ የሚያደርገው በችግሩ ውስጥ የመንግስትን ስልጣን ሽፋን የሚያደርጉ ሰዎች መኖራቸው ነው ያሉ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞች የክልልና ፌደራል መንግስታት ድርጊቶቹን ለማውገዝ ድፍረት ማጣት ትልቅ ችግር መሆኑን አስምረዋል፡፡ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመንተራስ ብሄር ተኮር ግጭቶች በቅርብ ጊዜ መቆም የሚችሉ አለመሆናቸውን ምናልባትም ተባብሰው ሊቀጥሉ የሚችሉበት እድል ስለመኖሩ እይታቸውን አጋርተዋል፡፡

አቆ ታደስ መለሰ (Metekel: Post 2018’s Political Change and the Conflict Dynamics) የመተከል አከባቢ ደሮም ቢሆን ግጭት የነበረበት እንደሆነ ነገር ግን ድሮ የነበሩት ግጭቶች በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩና የብሄር ቅርፅ ያልነበራቸው ናቸው ያሉ ሲሆን፡ አሁን ግን ግጭቶቹ የብሄር ቅርፅ እንዲይዙ ተደርገዋል ብለዋል፡፡

መተከል እና አከባቢው ብዙና የተለያዩ ማንነቶች በጋራ አብረው የሚኖሩበት አከባቢ መሆኑን አስረድተው፡ይሄ በዋናነት የሆነው በደርግ ዘመን በነበረው የሰፈራ ፕሮግራም አማካኝነት ከሌሎች ቦታዎች የተለያዩ ማህበረሰቦች ወደ መተከል በመምጣታቸውን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ግን የፌደራል ስርአቱ ክልሎችን ሲያዋቅር የነባርና ነባር ያልሆኑ ማህበረስብ ክፍፍል መፍጠሩ አሁን ለምናያቸው ችግሮች መነሻ ነው ብለዋል፡ በተለይ በቁጥር ሰፊ ሆነውና አከባቢው ላይ ነባር የሆነው አማራና አገው ምንም አይነት ፖለቲካዊ ውክልና አለማግኘቱ፡ ባስ ሲልም ከአከባቢው ለማፈናቀል የሚደረጉት ጥረቶችና እንቅሰቃሴዎች አከባቢዎች የቀውስ ቀጠና እንዳደረጉት ተናግረዋል፡፡

አከባቢው የልማት ኮሪደር እየሆነ መምጣቱ፡ ትልልቅ አገራዎ ፕሮጀክቶች መኖራቸውና የውጭ ሃይሎች ፍላጎትም የታከለበት የጥቅም ግብግም ይስተዋላል ያሉት ጥናት አቅራቢው በአከባቢው ያሉ ግጥቶች ከነዚህ የጥቅም ግብግቦች ተነጥለው የሚታዩ እንዳልሆኑ ገልፀዋል፡፡ የመንግስት አውቃቀሩ፡ የመሰረተ ልማት ችግር የሚመለከታቸው አካላት ግዴለሽነት ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ጋር ታክሎበት የችግሩን ግዝፈት እየጨመሩት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡  እንደመፍትሄም የአጭርና ረጅ,ም ጊዜ መፍትሄ ነው ያሉትን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ምግባሩ አያሌው (Conflicts in Ethiopia since the reform and the way outs)

ተቋሙ በእንደዚህ አይነት አጀንዳዎች ላይ መድረክ ማዘጋጀቱ የሚደነቅ እንደሆነ በመግለጽ መፍትሄ የለለው ችግር የለም፡ ስለሆነም ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እውቀት ተኮር መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በፅንስ ሃሳብ ደረጃ ግጭት በራሱ የሚወገዝ ነገር እንዳልሆነ፡ ተፈጥሯዊም እንደ መሆኑ ከግጭት ማምለጥ የማይቻል መሆኑን ነገር ግን ግጭቶችን የምናስተናግድበት መንገድ የግጭቱን ጥቅምና ጉዳት ይውስናል ብለዋል፡፡ በምሳሌነትም የሃሳብ ግጭትን አስፋላጊነት አንስተው ጠቃሚም ጎጂም የሚሆነው ነገሩን በምናስተናግድበት መንገድ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

በአራችን ታሪክ የሃብት ፉክክርን (Resource competition) መሰረት ያደረጉ ተለምዷዊ ግጭቶች የነበሩ ናቸው፡ ካሉ በኋል አሁን ላይ ግን የግጭቶቹ ተፈጥሮ እየተቀየረ ነው ብለዋል፡፡ ለነዚህም ዋና ምክንያቶች የብሄር ተኮር ትርክቶች፡ በዋናነት ደግሞ የግጭት ፈጣሪዎች (Conflict Entrepreneurs) ሚናተነስቷል፡፡

በጠቅላላው ካየነው ግን የግጭቶች መነሻ ፖለቲካዊ ውክልና፡ ሃይማኖት፡ የፖለቲካ ትርክቶች ሲሆኑ በዋናነት የሃገራችንን ችግሮች የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ህውሃት ወለድ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡ ህውሃት የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂውን ለማሳካት የብሄር ፌደራሊዝምን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል፡ በዚህም ለየ ብሄሩ ትርክቶች በመፍጠሩ በብሄሮች መካከል መጠራጠርና አለመተማመን በመፍጠር ብሄር ተኮር ችግሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

ለነዚህ ችግሮች እንደ መፍትሄም የድርጊታዊ (Operational) ና የመዋቅራዊ (Structural) መፍትሄዎችን የጠቆሙ ሲሆን ድርጊታዊ በሚለው አምድ ስር ምክክር፡ ውይይት፡ ቀልጣፋ አስተዳደራዊ ርምጃዎች፡ ቀልጣፋ ምላሽ፡ የግጭት ቅድመ ግምትና ትንተና ተቋማት አስፈላጊነትን እንደ መፍትሄ ያስቀመጡ ሲሆን መዋቅራዊ መፍተሄ ብለው የዘረዘሯቸው ደግሞ የዲሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር፡ የህግ የበላይት፡ የጋራ ማንነትን የሚያጎሉ ስራዎች መስራት (ኢትዮጲያዊነት)፡ የስላም ንቅናቄዎችን ማበረታታት (Peace activism): እንዲሁም ህገ መንግስት ማሻሻል ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡

የታዳሚዎች ተሳትፎ

አዳራሹ ውስጥ ክተለያዩ ት/ክፍሎች የመጡ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን በመወያያ ነጥቦች ላይ የተለያዩ ጥያቄና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡ ለምሳሌ የብሄር ግጭት የሚለው ቃል ብሔር ተኮር ተብሎ ቢያዝ የተሻለ ነው፡ ምክንያም ብሄሮቹ ወይንም ማንነቶቹ ሳይሆኑ የሚጣሉት እነሱን ለግጭት መሳሪያ (instrumentalize) የማድረግ ነገር ነው ያለው፡ የብሄር ግጭት የሚለው ነገር የሚጋጩ ብሄሮች ሳይሆኑ ያሉት ግብረ መልስ የለለው የአንድ ብሄር መፈናቀልና ጥቃት ስለሆነ የብሄር ጥቃት የሚለው ቃል የተሻለ ይገልፀዋል አይነት conceptual framing አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡ በተጨማሪም ችግሮቹ የተፈጠሩበት መዋቅርና አስተሳሰብ እያለ ከችግሮቹ መውጣት ይቻላል ወይ?ለጨቋጭ ተጨቋኝ ትርክት አቻና ተቃራኒ ትርክት መፍጠር አይቻልም ወይ? ብሄረተኝነት በብሄረተኝነት መዋጋት አዋጭ ነው ወይ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር፡ አዳራሹ ውስጥ ከነበረው የሞቀ ተሳትፎ አንጻር ሁሉም የመጠየቅ አስተያየት የመስጠት ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ከነበረው የጊዜ ማነስ የተነሳ ጥያቄዎች እንዳይደጋገሙ በአጭር አገላለጽ በመጠየቅ እድሉ ለብዙ ስው ለማዳረስ መድረኩን ጥረት ተደርጓል፡፡ 

ምሁራኑ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ የየራሳቸውን መልስ ከሰጡ በኋላ መድረኩን የሚመሩት ዶ/ር ፍሬው ይርጋለም ተሳታፊዎችንና ፓናሊስቶችን በማመስገን የእለቱን ውይይት ማብቃት አሳውቀዋል፡፡

 

በመጨረሻም በማህበራዊ ሳይንስ ፋካልቲ ዲን አቅራቢነት ውይይቱን በንግግር እንዲዘጉ የተጋበዙት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ መሰል መድረኮች ሲዘጋጁ ሊወሰድ ስለሚገባውየጊዜ አጥቃቀምና አያያዝ ላይ ገንቢ አስተያት ከሰጡ በኋላ ለጥናት አቅራቢዎቹ፡ ታዳሚዎችና አዘጋጅ ክፍሎች ምስጋናቸውን አቅርበው፡ መሰል መድረኮችን ይበልጥ አጥናክሮ ማስቀጥል እንደሚገባ እንዲሁም ከምሁራን ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን (Practitioners) ማሳተፍ እንደሚገባ ፡ ከሚነሱ አጀንዳዎች ጋር የሚያያያዙ ተቋማትን መጥራትና የውይይቱ አካል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በአፅንኦት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም እንደዚህ አይነት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማንኛውም አይነት ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልጽው ለተሰሩ ስራዎች ምስጋናቸውን ችረዋል፡፡ 

Share