የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት የገና በዓልን ከተማሪዎች ጋር በጋራ አከበሩ

08 Jan, 2026

ታሕሳስ 29/2018ዓ/ም (ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ) ፤ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር መንገሻ አየነ በዩኒቨርሲቲው ግቢዎች ለተማሪዎች በተዘጋጀው የገና በዓል ልዩ የምሳ ፕሮግራም ላይ በመገኘት በዓሉን ከተማሪዎች ጋር በቤተሰባዊ ስሜት አክብረዋል። ፕሬዚደንቱ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች ለተማሪዎች የተዘጋጀውን የምሳ መርሃ ግብር ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን በበዓሉ ዕለት ከተማሪዎች ጎን በመሆን ደስታቸውን ተካፍለዋል።
በተለይም በፖሊ፣ በፔዳ፣ በሰላም እና በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ግቢዎች በተከናወነው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል። የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ፕ/ር እሰይ ከበደ፣ የፕሬዚደንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አራጋው ብዙዓለም እና የውስጥ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማው አሸብር ከፕሬዚደንቱ ጋር በመሆን በዓሉን ከተማሪዎች ጋር አሳልፈዋል።
ዶ/ር መንገሻ አየነ በዚህ ወቅት ለመላው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ሠራተኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በዓሉን በግቢ ውስጥ ያከበሩ ተማሪዎችም በበኩላቸው፣ ከፍተኛ አመራሮችና ፕሬዚዳንቱ በመካከላቸው ተገኝተው አብረዋቸው በመመገባቸውና በዓሉን በማሳለፋቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው የሚሰማቸውን የብቸኝነት ስሜት እንዳስረሳቸውና ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ ለተማሪዎችና ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በሙሉ እንኳን ለገና በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
imageimageimage