ኮሌጁ ዓመታዊ ኮንፈረንስ አካሄደ

 የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ከአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር “Agriculture and Environmental Management for Sustainable Development” በሚል ርዕስ ጉዳዩ ላይ ሶስተኛውን ዙር ዓመታዊ አገር አቀፈ ኮንፈረንስ በኮሌጁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለሁለት ተከታታይ ቀናት አካሄደ፡፡

መርኃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቅረሰላም ጋረድ ጥሪውን አክብረው ለመጡ ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ዩኒቨርሲቲው በ2017 በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ 10 ምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ጐራ ለመሰለፍ የሰነቀውን ራዕይ ለማሳካት በርካታ አኩሪ ተግባራት እያከናወነ እንደሆነና ራሱን ከማስፋፋት አንፃርም በየአቅጣጫው አዳዲስ ግቢዎችን በማስገንባት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ የመማር ማስተማሩን ሂደት በተሳካ መንገድ ከማካሄዱም ባሻገር በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት የሥራ ዘርፎችም ይበል የሚያሰኙ ሥራዎች እያከናወነ ሲሆን ኮሌጆችም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ጠንክረው በመሥራት ላይ ስለሆኑ የኮንፈረንሶች መካሄድ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

ም/ፕሬዚዳንቱ አክለውም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር ኮሌጁ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ደሳለኝ ሞላ የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ ሙህራን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በርካታ ችግር ፈች የምርምር ሥራዎችን ስለሚያቀርቡ አንዱ ከሌላው ልምድ ቀስሞ ለወደፊት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ነጥሎ በማውጣት የመፍትሄ አቅጣጫ የሚሰጥበት የምክክር መድረክ እንዲሆን ታልሞ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዲኑ አያየዘውም የቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎችና ባለቤቶች ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከኮሌጁ መምህራን ስለሆኑ ለሰሩት ማበረታቻ ሲሆን ለቀሪዎች ደግሞ የማንቂያ ደወል እንደሚሆን አስገንዝበው ከሀገር ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ሙህራንም ስለተጋበዙ ኮንፈረንሱ ለፖሊሲ አውጭዎች ብሎም ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች ለኮንፈረንሱ ድምቀት የሰጡት የእስራኤል አምባሳደር በኢትዮጵያ የክብር እንግዳ የሆኑት አምባሳደር በላይነሽን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ሙህራን፣ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች፣ የኮሌጁ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች ሲሆኑ ከኮንፈረንሱ ብዙ ነገሮችን መገንዘብ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤም በበኩላቸው ግብርና ለአንድን ሀገር ኢንዱስትሪ ዋና አሽከርካሪ ሞተር ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግና የሀገሪቱን ምርትና ምርቃትነት ለማሳደግ በጠባብ ቦታ (መሬት) ላይ ብዙ ምርት ለማምጣት የሚያስችል እውቀት ለመቀመር ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ሁሉ ሰፊ መሬት መረከብ ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው የምርቱን ዘለቄታማነትና ተያያዥነቱን የሚከታተል ኢንዱስትሪ ማቋቋም ተገቢ ስለሆነ ኮሌጁ ደግሞ በርካታ ሙህራኖችን አቅፎ የያዘና የግብርና ምርምሮች በሰፊው የሚሰሩበት ስለሆነ ለወደፊት ከፍተኛ የሆነ የምርምር ተቋም ይሆን ዘንድ ዩኒቨርሲቲው ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል! ታዳሚው በሁለት ቡድን በመከፋፈል ሰፊ ውይይት አካሂዶ አወያዮችም አጥጋቢ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡