የልጃገረዶች የሳይንስ ካምፕ (STEM Girls Camp) ፍፃሜ አገኘ

 

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ማበልፀጊያ ማዕከል (STEM Center) በየዓመቱ የሚያካሂደውን የልጃገረዶች የሳይንስ ካምፕ(STEM Girls Camp) ስልጠናና ውድድር በፔዳ ግቢ ለ8 ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ ለአሸናፊዎች የተለያዩ ሽልማቶችን በማበርከት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

በመዝጊያ ፕሮግራሙም የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ ም/ፕሬዘዳንት እና በአሁኑ ስአት ደግሞ የአብክመ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበን እና የከተማውን የትምህርት መምሪያ ም/ኃላፊ አቶ መላክ ጀመረን ጨምሮ  የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮምኒኬሽን ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተገኝተዋል፡፡

ዶ/ር ዘውዱ እምሩ በእግር ኳስ ጨዋታው ላሸነፉት ለፕሮፌሰር የአለምፀሀይና ለፕሮፌሰር ሶስና ቡድኖች ዋንጫ ከአበረከቱ በኋላ በመልዕክታቸው ተማሪዎች ወደ መጡበት ት/ቤት ሲመለሱ የቀሰሙትን እውቀት ለሌሎች የትምህርት አጋሮቻቸው እንዲያካፍሉና በያዙት ላይ ተጨማሪ እውቀት በመገብየት ለሞዴልነት የተጠቀሱትን ታዋቂ ሴት ሳይንቲስቶች በመተካት አገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው በአጠቃላይ ቆይታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡት ለዶ/ር ደብረወርቅ ቡድኖች የአንደኝነትን ማዕረግ የሚገልፀውን ዋንጫ አበርክተው በተማሪዎች መካከል የሚደረገው ፉክክር የወደፊት ታላቅነታቸውን እንደሚያሳይና ሳይንቲስቶችን እንደሚተኩ የሚያመላክት ነገር እንዳለ ጠቁመው ዕቅድ፣ጠንክሮ መስራትና ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በቁርጠኝነት መታገል ለከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደርስ አስገንዝበዋል፡፡

አቶ መላክ የምስክር ወረቀት ለቡድን ተወካዮች ከሰጡ በኋላ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው እያበረከተ ያለውን ጉልህ አስተዋፅኦ አመስግነው ለወደፊቱም ድጋፉና ክትትሉ እንዳይለይ በማሳሰብ ቢሮአቸው ይህን የመሰሉ ትውልድ የመቅረፅ ስራዎች ላይ በጋራ የመስራት እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በተማሪዎች መካከል የእግር ኳስ እና የዱላ ቅብብል ጨዋታ ውድድር፣ስነ ፅሁፍና የቆይታ ሪፖርት ቀርቦ የምስክር ወረቀትና ለአሸናፊ ቡድኖች የዋንጫ ሽልማት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡

ተማሪዎች ፕሮግራሙ እጅግ በጣም ጥሩ መሆኑን ገልፀው ለሌሎች እድሉን ላላገኙት የክፍል ጓደኞቻቸው ተደራሽነቱ እንዲሰፋ እንዲሁም ቀጣይነት እንዲኖረው በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡