ኮሌጁ የትምህርት ቤቱን አቅም ለማጎልበት ቆርጦ መነሳቱ ተገለፀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ለባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ዘንዘልማ የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት የተለያዩ የትምህርት መረጃ መሳሪያዎችን የርክክብ ስነ-ስርዓት አካሄደ፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ደሳለኝ ሞላ የዛሬው የመጀመሪያ በር ከፋች ስጦታ እንደሆነና ለወደፊቱ ዩኒቨርሲቲው ብሎም ኮሌጁ ትምህርት ቤቱን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ትኩረት ሠጥቶ እንደሚሠራና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ የኮሌጁ አቅም እስከፈቀደ ድረስ ከትምህርት ቤቱ የበላይ አመራሮች ጋር በመነጋገር ልዩ ልዩ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ከተበረከቱት 10 ኮምፒውተሮች መካከል ሶስቱ ለትምህርት ቤቱ የበላይ አመራሮች የስራ ማከናወኛ እንዲሆኑና ቀሪዎቹ ተማሪዎች ከታች ክፍል ተኮትኩተው ማደግ ስላለባቸው የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉበት ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 የርክክብ ስነ-ስርዓቱን ያካሄዱት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ዓብይ መንክር ሲሆኑ የትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጠነክርና ተቋማዊ ለውጥ እንዲመጣ ድጋፉ ተገቢ መሆኑን ገልፀው ለስጦታ የቀረቡት ያገለገሉ 10 ኮምፒውተሮች፣ ያገለገለ አንድ ፕሪንተር፣ ሁለት ጠረጴዛዎች፣ 100 ደስታ ክላሴርና 10 ደስታ ወረቀት እንዲሰጡ ላደረጉት አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበው ዩኒቨርሲቲው  እያከናወናቸው ካሉት 3 ዓብይ ተግባራት ውስጥ አንዱ የማህበረሰብ አገልግሎት እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ዘርፎች ለትምህርት ቤቱ የሚደረጉ ድጋፎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አሳስበው ለትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ተክለወልድ ብርሃኔ አስረክበዋል፡፡

 በርክክቡ ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ የትምህርት ጥራትና ኢንስፔክሽን ባለሙያ አቶ ጋሻው በላይ ትምህርት ቤቱ ምንም ነገር ሳይሟላለት በርካታ ተግዳሮቶችን በውስጡ ይዞ የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያከናውን በመሆኑ ለተደረገው ድጋፍ ታላቅ ምስጋና አቅርበው ካለው ችግር አንፃር ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው አሳስበዋል፡፡

 አቶ ተክለወልድ በበኩላቸው ምንም እንኳ ለሥራው አዲስ ባይሆኑም ከቦታው ግን ቅርብ ጊዜ የተመደቡ መሆኑን ገልፀው እሳቸው ሲመጡ ድጋፍ የሚያደርግ አካል በመገኘቱ እድለኛና ደስተኛ መሆቸውን ገልፀው የትምህርት ቤቱን ጉልህ ችግር ትኩረት ሰጥቶ ለርዳታ ዝግጁ የሆነውን ዩኒቨርሲቲውን  ካመሰገኑ በኋላ ትምህርት ቤቱ ለወደፊት ተስፋው የለመለመ መሆኑን የሚያመላክት ስጦታ እንደተበረከተላቸው ገልፀዋል፡፡