በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም 7ኛው አገር አቀፍ አመታዊ የምርምር ጉባኤ እየተካሄደ ነው

"መራመድ እንጂ ስለ እርምጃ ማውራት አስፈላጊ አይደለም" ምንተስኖት አዘነ (ዶ.ር)
ባሕረ ዳር፡ ሕዳር 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም፤ በማስረጃ ላይ በተደገፈ ጥናት ችግሮች የተፈቱለት ማኅበረሰብ መገንባት በሚቻልበት ዙሪያ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር መክሯል።
የአየር ንብረት ለውጥና ግብርናው ተለያይተው መታየታቸው ችግሮችን ለመፍታት አስቸጋሪ እንደሆነ በውይይቱ ተነስቷል። አጥኚዎች የአየር ንብረት ለውጥ እና ግብርናውን ወደ አንድ ተቋም አምጥቶ ችግሩን መቀነስ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በምክክሩ የተገኙት በአመልድ ኢትዮጵያ የአይበገሬነት የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ መኳንንት ዳኘው፤ የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን በጥናት መደገፍ መልካም ነው ብለዋል። የተሻለ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በጥናት የተመሠረተ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ለማኅበረሰብ ለውጥ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም ነው የገለጹት።
በምክክሩ ጥናት ያቀረቡት ፕሮፌሰር በላይ ስምዓኒ የኢትዮጵያን ግብርና የጎዳው የሕዝብ ቁጥር መጨመር መሆኑን አንስተዋል። በኢትዮጵያ ከ75 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ግጭቶች የሚነሱት በሀብት ይገባኛል መሆናቸውን የሚያነሱት ፕሮፌሰሩ ጥቅም የሚባለው ደግሞ የመሬት ይዞታ እና ሌሎች ናቸው ይላሉ። በኢትዮጵያ አሁን የሚታረሰው መሬትና ቴክኖሎጂ ከሕዝቡ ጋር ተመጣጣኝ አይደለም ነው ያሉት።
ለችግሮች ሁሉ አንድ አይነት የሆነ መፍትሔ ማግኘት አይቻልም ያሉት ፕሮፌሰር በላይ፤ ለብዙ ችግሮች የበዙ መፍትሔዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።
ለም መሬት ይዞ የሚራብ ሕዝብ ማየት ሊያም እደሚገባ ተናግረዋል። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ይጨምራል ያሉት ፕሮፌሰሩ ሕዝብ በጨመረ ቁጥር የፖሊሲ ለውጥ ካልተደረገ አደጋው የከፋ እንደሚሆንም አንስተዋል። በኢትዮጵያ ሕዝብ እየበዛ መሬት እየጠበበ እየሄደ መሆኑን ተናግረዋል። እየበዛ የሄደውን ሕዝብ ለመመገብ ጦም የሚያድረውን መሬት በስፋት ማልማት እንደሚገባም አመላክተዋል።
እየተጎዳ ያለውን መሬት መጠበቅና ምርትና ምርታማነትን መጨመር ግድ እንደሚልም ገልጸዋል። በግብርናው እና በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚደረገው የጥናት ባሕል መቀየር እንደሚገባውም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የሚሠሩት ጥቂት ናቸው፣ ጥናት የሚያደርጉት ግን በርካታ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር በላይ ጥቂት ጠቃሚ ጥናቶች እና በርካታ ሠራተኞች ያስፈልጉናል ነው ያሉት።
ለአብነት እምቦጭ ላይ የሚያጠና አጥኚ እምቦጭ በሐይቁ ላይ ምን ያክል ጨምሯል ሳይሆን እምቦጭን እንዴት እናጥፋው በሚለው ላይ መሆን አለበትም ብለዋል። የሚቀርቡ ጥናቶች ከቋንቋቸው ጀምሮ ለማኅበረሰቡ የቀረቡ አለመሆናቸውንም ገልጸዋል። በግብርና ዘርፍ የሚሰጠውን ትምህርት ማሻሻል እንደሚገባም ተናግረዋል። የእድገት ፍላጎትና የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ የማይመጣጠን ከሆነ ለውጥ እንደማይመጣም ገልጸዋል።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ምንተስኖት አዘነ (ዶ.ር) የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። የማኅበረሰብ አገልግሎቱና ሌሎች ሥራዎችን ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም እንደሚሠሩ ገልጸዋል። ከማኅበረሰቡ እውቀት በመነሳት ለማኅበረሰብ የሚጠቅም ነገር መሥራት መቻል እንደሚገባም ተናግረዋል።
የማኅበረሰቡን አደረጃጀት በማክበር በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። ከአካባቢ የሚገኙ እውቀቶችን መጠበቅና በእነርሱ ላይ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት። ዪኒቨርሲቲው ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።እርምጃን መራመድ እንጂ ስለ እርምጃ ማውራት አስፈላጊ አይደለም ያሉት ዶክተሩ ጥናቶችን ተግባራዊ ማድረግ ግድ ይላል ብለዋል።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት የታገዘ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምግብ እጥረት ያስከትላል፣ የምግብ እጥረት ሲከሰት ሌሎች ችግሮች እንደሚመጡ ነው የተናገሩት። ማኅበረሰብ ተኮር የሆነ የአደጋ መከላከል ላይ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
 
 
Share