አገር አቀፍ የስርዓተ ትምህርት ግምገማ አውደ ጥናት ተካሄደ ******************************************************

አገር አቀፍ የስርዓተ ትምህርት ግምገማ አውደ ጥናት ተካሄደ
******************************************************
(ሀምሌ23/2014ዓ.ም፣ባሕርዳርዩኒቨርሲቲ-BDU) የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም "BSc Degree in Occupational Safety Risk and Environment" ወይም "የሳይንስ ባችለር ዲግሪ በስራ አካባቢ የአደጋ ስጋት ደህንነት "የተሰኘ አዲስ ትምህርት ክፍል ለመክፈት አገር አቀፍ የስርዓተ ትምህርት ግምገማ አውደ ጥናት አካሄደ፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ምንተስኖት አዘነ እንደገለጹት አዲስ ሊከፈት የታሰበው ትምህርት ክፍል በአገር አቀፍ ደረጃ በሰውና ንብረት ላይ የሚከሰተውን ስጋት ለመቀነስና ምቹ የስራ ቦታ ለመፍጠር የሚያስችል የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ታልሞ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በአገሪቱ ያለውን የአደጋ መከላከልና ዘላቂ ልማትን ከግብ ለማድረስ የትምህርት ክፍሉ መከፈት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ ክጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ኤክስኪዩቲቪ ዳይሬክተር ዶ/ር ዳዊት አስራት በበኩላቸው የተቋሙ አመሰራረት ምን ይመስል እንደነበር አውስተው በቅርቡ የተመሰረተ ቢሆንም ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መቻሉ አበረታች ስራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ዳዊት በማስከተል አዲስ ሊከፈት የታሰበው ትምህርት ክፍል በአገር አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት ስለሚገኝ የዩኒቨርሲቲውን ከፍታ እንደሚጨምርና ተቋሙም ዩኒቨርሲቲው ትኩረት እንዲሰጠው ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የስርዓተ ትምህርቱን ረቂቅ በፅሁፍ ያቀረቡት የተቋሙ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አብርሃም መብራት ተቋሙ በ2005 ዓ.ም እንደተመሰረተና በአጭር ጊዜ ተጠናክሮ ሰፊ ስራዎችን በማከናዎን ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማስከተል አዲስ ሊከፈት በታሰበው ትምህርት ክፍል የሰለጠነ የሰው ኃይል ቢኖር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰተውን አደጋ ለመቀነስ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስገንዝበው የተቀረፀው ስርዓተ ትምህርት አስፈላጊነቱ፣ በውስጡ ያሉ የትምህርት ዓይነቶች ምን እንደሚመስል እና አጠቃላይ ይዘቱን በፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
የቀረበውን ረቂቅ ጠንካራ ጎን በማውሳት አንዳንድ መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች በፅሁፋቸው የጠቆሙት ደግሞ ዶ/ር መታደል አዳነ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ዶ/ር አውራጃው ደሴ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተጋባዦች ናቸው፡፡
በመርሃ-ግብሩ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የተቋሙ መምህራንና ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች የታደሙ ሲሆን በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የመርሃ-ግብሩን ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ተከታታይና የርቀት ትምህርት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር አበበ ድረስ መርሃ ግብሩን ላዘጋጀው አካል፣ ለፅሁፍ አቅራቢዎች እና ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለመጡ ታዳሚዎች ምስጋና አቅርበው የትምህርት ክፍሉ መከፈት ይበል የሚያሰኝና የዩኒቨርሲቲውን ገፅታ ከሚገነቡት ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር አበበ አክለውም የፕሮግራሙ መከፈት በአይነቱ ለየት ያለ በመሆኑ ተቋሙ የተሰጡትን አስተያየቶች አካቶ ስርዓተ ትምህርቱን እንዲያፀድቅና ትምህርት ክፍሉ መከፈቱን በሰፊው እንዲያስተዋውቅ አሳስበዋል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ-BDU
ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ

Share