ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ከ7.6 ሚሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር አገኘ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ከ7.6 ሚሊየን
በላይ የአሜሪካ ዶላር አገኘ

(ሐምሌ 27/2014ዓ.ም፣ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ-BDU) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ #የአደጋ #መከላከልና #ምግብ #ዋስትና #ጥናት #ተቋም ለUSAID ያቀረበው የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ተቀባይነት አግኝቶ 406.9 ሚሊየን ብር ወይም 7,678,943.00 የአሜሪካ ዶላር አግኝቷል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምር/ማህ/አገ/ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው የፕሮጀክቱን ዓላማና የተገኘውን ገንዘብ በተመለከተ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ የአምስት አመታት የቆይታ ጊዜ እንደሚኖረውና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ #የአደጋ #መከላከልና #ምግብ #ዋስትና #ጥናት #ተቋም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ሲሆን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም በ5ዓመታት ቆይታ ጊዜውም በየሁለት አመቱ 150 ተማሪዎችን በተዘጋጀው ዝርዝር የምልመላና ምዘና መስፈርት መሰረት አወዳድሮ ወደ ፕሮጀክቱ የሚያስገባ ሲሆን በአምስት አመት የቆይታ ጊዜውም በድምሩ 750 ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ሦስት ዓላማዎች ያሉት ሲሆን በአደጋ ስጋትና መከላከል ዙሪያ ለ750 ሰዎች በተግባር የተደገፈ ስልጠና ሰጥቶ ብቁና ተወዳዳሪ አመራርና ባለሙያ እንዲሆኑ ማስቻል ፣ በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ውስጥና ተዛማጅ ተቋማት ውስጥ እየሰሩ ያሉ አመራሮችን ችሎታ አሳድጎ በቀጣይነት ብቁ አመራሮች አድርጎ ማውጣት እና ከዚህ ፕሮጀክት ሰልጥነው የሚወጡ ወጣት ተማሪዎች በሙያቸው ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው በሌሎች ተቋማት መቀጠር እንዲችሉ ማድረግ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም በስልጠናቸው ጊዜ በትኩረት ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች የሚተገበር ሲሆን ከየክልሉ ፕሮጀክቱን ለማስተባበር የተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በየክልሉ እንዲተገበር ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያነት የተገኘው ገንዘብ በፕሮጀክቱ ታቅፈው ለሚሰሩ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች እውቀትና ልምድ እንዲያገኙ እንዲሁም በገንዘብ እንዲደገፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ተማሪዎችንም በተግባር ልምምድ የተደገፈ ስልጠና ሰጥቶ ውጤታማ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እንዲሰሩ የሚያስችል ስለመሆኑም አክለው ተናግረዋል፡፡

Share