የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ስልጠና ሰጠ

የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ስልጠና ሰጠ
******************************************************
(ሀምሌ 20/2014 ዓ.ም፣ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-BDU) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ከሰሜን ሜጫ ወረዳ እና በስሩ ከሚገኙ 38 ቀበሌዎች ለተውጣጡ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በአደጋ ስጋት መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ በዱር ቤቴ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
የስልጠናው አስተባባሪ በአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም የትምህርት ጥራትና ቁጥጥር አስተባባሪ አቶ አሳየ ይስማው እንደገለጹት በወረዳው በጣለው ከባድ በረዶ ምክንያት የደረሰውን አደጋ በተመለከተ የዩኒቨርሲቲው የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ሦስት ቀን የወሰደ ዝርዝር የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል፡፡ በተካሄደው ጥናትም በአደጋ መከላከል ላይ የቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት የታየ ሲሆን ተናቦና ተቀናጅቶ የመስራት ችግርን በሳይንሳዊ መንገድ እንዴት መፍታት እንደሚቻል ጥናት ከተደረገ በኋላ ስልጠናው እንደተዘጋጀ የስልጠናው አስተባባሪ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ሜጫ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አንተነህ ወንዱ በበኩላቸው በወረዳው ሰኔ 4 እና ሰኔ ዘጠኝ ቀን በጣለው በረዶ የቀላቀለ ዝናብ የደረሰውን አደጋ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተዘዋውረው በመመልከት ለዚህ ችግር መፍትሄ በማፈላለግና ማህበረሰቡ የደረሰበትን ችግር ሊፈታ የሚችል ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም ጉዳት የደረሰበት ማህበረሰብ ድረስ ወርዶ በመመልከት ማህበረሰቡን የማወያየትና የተረጋጋ ኑሮውን እንዲቀጥል የማድረግ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
በወረዳው በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዘነበው ከባድ በረዶ በንብረት፤ በመኖሪያ ቤቶች እና በሰብል ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ችግር ለመፍታት የተለያዩ ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን በግንባር ቀደምትነት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ ቦታው ድረስ በመገኘት ችግሩን ተረድቶ ለመፍታት ተንቀሳቅሷል፡፡ ላበረከተው አስተዋፆም አቶ አንተነህ በሰሜን ሜጫ ወረዳ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በወረዳው የደረሰውን አደጋ ለመፍታት የተለያዩ አብይና ንዑስ የቴክኒክ ኮሚቴዎች የተቋቋሙ ቢሆንም ባጋጠመው የእውቀት ክፍተት የቀረቡ እርዳታዎችን በፍትሀዊነት ተደራሽ የማድረግ ችግር አጋጥሞ ነበር ይህን ችግር በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት የዛሬው ስልጠና በጣም አስፈላጊ መሆኑን የወረዳ አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሙሉነህ ጌታነህ ሲሆን የአደጋ መከላከል ማስተባበሪያ ሥርዓት በምን መልኩ ሊቋቋም ይገባል፤ የቅድመ አደጋ ክስተት እንቅስቃሴዎች ምን ይመስላሉ፤ አደጋው በተከሰተ ጊዜ እንዴት ይፈታ፤ አደጋው ከተፈጠረ በኋላ ምን መደረግ አለበት፤ በአደጋ ጊዜ የሀብት አስተዳደርና አጠቃቀማችን ምን መምሰል አለበት በሚሉት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ-BDU
ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ
Wisdom at the source of Blue Nile

Share