ለባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የምህንድስና መምሪያ ጋር በመተባበር በፋብሪካው ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች ለሚሰሩ ሰራተኞች አደጋን በመከላከል ላይ ያተኮረ የስራ ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የሰው ሀብት ስልጠና ባለሙያ አቶ አሁንም ካሳ ስልጠናው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በፋብሪካው የምህንድስና መምሪያ በጋራ በመሆን እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው ሰልጣኞች ከሽመና፣ ፈትል፣ ማቅለሚያና ማጠናቀቂያ ምህንድስናና መሰል መምሪያዎች የተወጣጡ ባለሙያዎች እና የፋብሪካው የእሳት አደጋ ሰራተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በስልጠናውም አደጋ ሲከሰት እንዴት መከላከል እንዳለባቸው እንዲያውቁ መደረጉን ገልጸው ድርጅት እንደመሆኑ መጠን እሳት በእፍግታ አማካኝነት ሊከሰት ስለሚችል የአደጋውን መጠን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አደጋ መከላከል ትምህርት ክፍል መምህርና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ሄኖክ አባተ ስልጠናው የሚያተኩረው አደጋ ሲከሰት አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠትና በአደጋ የተጎዱትን ወደ አገልግሎት መመለስ እንዲቻል ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ አስተባባሪው አክለውም ብዙ ድርጅቶችንም የማብቃት፣ ድጋፍና ክትትል የማድረግ ሃላፊነት ተቋሙ እንዳለበት ጠቁመው ጥናት በመስራት ከባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ባለሙያዎች ጋር እየተሰጠ ያለው ስልጠና ለሰልጣኞች በተለይም በኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚፈጠሩ የእሳት አደጋዎች ግንዛቤ በማስጨበጥ እና እንዴት መሳሪያዎችን በመጠቀም የእሳት አደጋን መከላከል እንደሚቻል በማሰልጠን ሊከሰት የሚችለውን የንብረትና የህይወት ውድመት ማስቀረት እንደሚቻል ተናግረዋል።አቶ ዮሴፍ ታምሩ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አደጋ መከላከል እና ቀጣይ ልማት ተቋም መምህር የስልጠናው አስፈላጊነት በተቁሙ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እና በፋብሪካው የሚመለከታቸው አካላት ጥናት እንደታወቀ ጠቅሰዋል፡፡ በፋብሪካው ውስጥም የእሳት አደጋ መከላከያ መሳሪያዎች ቢገኙም ብዙ ሰራተኞች እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ባለማወቃቸው ምክንያት አደጋን ለመከላከል እንደሚቸገሩ አውስተዋል፡፡ አቶ ዮሴፍ ስልጠናው ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረው የእሳት አደጋን ለመከላከል ሁሉም ሰራተኞች ቢሰለጥኑ በአቅራቢያቸው ሊከሰት ለሚችል አደጋ ደራሽ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
ስልጠናው እየተሰጠ ያለው በአቶ ሄኖክ አባተ፣ በአቶ ዮሴፍ ታምሩ እና በ3 የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እየተሰጠ ይገኛል።

Share