የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ የታዳጊ ህጻናት ሳመር ካምፕ የመዝጊያ መርሃ ግብር በደመቀ ሁኔታ ተካሄደ
Peda Campus
06 Sep, 2026
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ለሁለት ወራት በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የቆየውን 753 ታዳጊ ህጻናት የሳመር ካምፕ ስልጠና የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ወላጆች፣ ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና እንግዶች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል።

BDU Sport Academy Summer Sports camp 2026 in training time
በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዲን አቶ ሲሳይ አዱኛ፣ የሳመር የስፖርት መርሃ ግብሩ ታዳጊዎች አካላዊ እድገታቸውን እንዲያሻሽሉ፣ የስፖርት ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ፣ በቡድን የመስራት ባህላቸውን እንዲጠናከር እና ክረምቱን በጤናማና አስደሳች መንገድ እንዲያሳልፉ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልጸዋል። በተጨማሪም ልጆች ለዲጂታል ዓለም አሉታዊ ተጽዕኖዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ትልቅ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል።
አቶ ሲሳይ አክለውም፣ በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ ህጻናት ደስተኛ፣ ጤናማ እና በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሁም አዳዲስ ጓደኞችን አፍርተው ወደ መደበኛ ትምህርት ቤታቸው ከፍ ባለ ተነሳሽነት የሚመለሱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ስፖርት አካዳሚው በበጋ ወራት 236 ታዳጊዎችን በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ማሰልጠኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመት በዋናው ግቢ 480 እና በዘንዘልማ ግቢ 37 ታዳጊዎች በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ስልጠና ማግኘታቸውን ገልጸዋል። በአጠቃላይ 753 ታዳጊዎች እንደየ እድሜአቸው ተመጣጣኝ ስልጠና እንዳገኙም አመልክተዋል።

Summer Sports Camp 2026 graduates
ከሰለጠኑት ህጻናት መካከል ተሰጥኦና ፍላጎት ያላቸው በልዩ መርሃ ግብር ተመርጠው ከሰኞ እስከ አርብ ከትምህርት በኋላ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ በቀጣይ ስልጠና እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
የአካዳሚው ዲን ስኬታማ የሆነው የሳመር ካምፕ መርሃ ግብር በአሰልጣኞች፣ በአስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ እንዲሁም በወላጆች ትብብር መሳካቱን ገልጸው፣ ልጆቻቸውን በእምነት ለአካዳሚው ለሰጡ ወላጆች ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።

summer sports camp 2026 coaches
በእለቱም ታዳጊ ህጻናቱ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ያገኙትን ክህሎትና ብቃት በአስደናቂ የስፖርት ትርኢቶች ለታዳሚዎች በማቅረብ የመዝጊያ መርሃ ግብሩን አድምቀውታል።