በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ስልጠና እየሰጠ ነው

ትዕግስት ዳዊት
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከአማራ ክልል የስፖርት ሳይንስ ሙሁራን ማህበር ጋር በመተባበር በመጀመሪያ እርዳታ እንዲሁም ማሳጅ አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የተግባር እና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉት በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ስፖርት መምህራን ሲሆኑ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተነሳሽነቱን በመውሰድ እና አሰልጣኞችን በማስመጣት ስልጠናውን እየሰጠ ይገኛል።
የአካዳሚው ም/ዲን አቶ ሲሳይ አዱኛ አማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የስፖርት ሳይንስ ሙሁራን ማህበር ከስፖርት አካዳሚ ጋር በጋራ በመሆን በክልሉ ለሚገኙ የስፖርት መምህራን ማሳጅ እና ቴራፒዩቲክ ሳይንስ በሚል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ ሲሳይ የስልጠናው ዋና አላማ ስፖርተኞች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚያጋጥማቸው ጉዳት ጊዜ በየአካባቢያቸው እንዴት መርዳት እንደሚቻል የንድፈ ሃሳብ እና የክህሎት ሰልጠና ወስደው ማህበረሰባቸውን ማገልገል እንዲችሉ ማስቻል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ሲሳይ አክለውም አማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የስፖርት ሳይንስ መምህራን ማህበር የክልሉ ማህበረሰብ በስፖርት የሚገባው ደረጃ ላይ አይገኝም ብሎ ያስባል ስለዚህም የክልሉ ማህበረሰብ በስፖርቱ ዘርፍ ካሰበው ደረጃ ይደርስ ዘንድ ከምሁራን ምን ይጠበቃል የሚል ጥያቄ በማንገብ ማህበሩን መስርቶ የክልሉን ስፖርት ከፍ ለማድረግ እየሰራ ያለ ማህበር ነው ብለዋል። ሰልጠናውን የሚሠጡትም በሃገሪቱ አሉ የተባሉ በክልሉ የሚገኙ ሁለት አሰልጣኞ ማለትም አቶ ዳንኤል ክብረት የብሄራዊ ቡድን የስነ ምግብ ባለሙያ እና በክሊኒካል ኒውትሪሽን ፒኤች ዲግሪ ተማሪ እና አቶ የሽዋስ ጀምበሩ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ትም/ክፍል ተጠሪ ፣በስፖርት ሜዲስን የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እንዲሁም በኢመርጀንሲ ሜዲካል ቴክኒሽያን “የድንገተኛ ህክምና ባለሙያ” ናቸው፡፡
አቶ ሲሳይ እንዳሉት ስፖርት አካዳሚው ለስልጠናው ተነሳሽነቱን በመውሰድ እና ለስልጠነው የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን በማሟላት ስልጠናው እየተሰጠ ይገኛል። አቶ ሲሳይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ የማህበሩን ለመመስረት የአንበሳውን ድርሻ የወሰደ እና ማህበሩ እውቅና አግኝቶ ወደስራ መግባት ደረጃ ላይ ያለ በመሆኑ ወደፊት የክልሉን ስፖርት ለማሳደግ ከማህበሩ ጋር በጥምረት እንሰራለን ብለዋል።
ስልጠናው ለ 10 ቀናት የሚሰጥ ይሆናል ነው የተባለው።