ስፖርት አካዳሚ የ1ኛ ደረጃ እግር ኳስ የአሰልጣኝነት ስልጠና ሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከባህር ዳር ከተማ ባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር በከተማው ውስጥ በልምድ ተነሳስተው ታዳጊ ወጣቶችን ለበርካታ ዓመታት በማሰልጠን ላይ ለሚገኙ 21 አሰልጣኞች ለ15 ቀናት የቆየ የ1ኛ ደረጃ የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ስልጠና ሰጠ፡፡
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የባሕር ደር ከተማ አስተደደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አሰፋ ለረዥም ጊዜ ሰልጣኞች ሲጠይቁት የነበረዉን ስልጠና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ስልጠናዉ እንዲካሄድ በማድረጉ ምስጋና አቅርበው ለሰልጣኞቹ ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የስፖርት አካዳሚ ዲን ዶ/ር ዳኛቸው ንግሩ ለሰልጣኞቹ የምስክር ወረቀት የመስጠት ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር “አቅም እያላችሁ የአሰልጣኝነት ወረቀት ባለመኖሩ እስካሁን ድረስ ለመለወጥ ዝቅ ብላችሁ በመስራታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል” ብለዋል፡፡ አክለውም አገር ወክለው የሚጫወቱ ወጣቶችን ለማፍራት ስለምትሰሩት ስራ አካዳሚው በተቻለው አቅም ሁሉ ለመደገፍ ይሰራል ሲሉ ዶ/ር ዳኛቸው ሰልጣኞችን አበረታተዋል፡፡
ሰልጣኞችም አካዳሚው ትኩረት ሰጥቶ ላደረገላቸው ቀና ትብብር ለኢንስትራክተር ጌታቸው ተሾመ፣ለአሰልጣኝ ዶ/ር ደኛቸዉ ንግሩ እና ለባህር ዳር ከተማ ባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ቴክኒክ ባለሙያ ለአቶ ሀብታሙ መኮንን ማበረታቻ የሚሆን የመፅሀፍት ሽልማት አበርክተዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን ዶ/ር ተከተል አብርሃም በበኩላቸው አካዳሚው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ እየሰጠ የሚገኘውን የአቅም ግንባታ ስልጠና አጠናክሮ በመቀጠል አገራችን እየተስተዋለ ያለውን የእግር ኳስ ውጤት ማጣት በዘላቂነት ለመቅረፍ የታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡