የሐይማኖቶች ጥናት አግባብነት እና ሀገራዊ ፋይዳ አውደ-ጥናት ተካሄደ

[ግንቦት 26/2014ዓ/ም፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ] የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ "የሐይማኖቶች ጥናት አግባብነትና ሀገራዊ ፋይዳ" በሚል መሪ ቃል በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሀገራዊ አውደ-ጥናት አካሄደ፡፡

አውደ-ጥናቱን አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዩች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ እንደገለጹት አገራችን ኢትዮጵያ በርካታ የሐይማኖት ብዝሀነት የምታስተናግድ አገር በመሆኗ ከአሁን ቀደም የክርስትናና የእስልምና ሐይማኖቶች በስፋት የነበሩ ሲሆን ማህበረሰቡም ተከባብሮ በፍቅር እንዲኖር ሐይማኖቶች ያላቸው ፋይዳ የጎላ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር እሰይ አክለውም በአሁኑ ወቅት መተሳሰቡን ወደጎን በመተው በሐይማኖቶች ልዩነት ምክንያት ጥላቻ እየተስተዋለ መሆኑን ገልፀው ፋኩልቲው ይህን ተግዳሮት ለመቅረፍ አንድ እርምጃ ወደፊት ሊወስድ የሚችል አውደ ጥናት ማዘጋጀቱና ሊከፈት የታሰበው የሐይማኖቶች ጥናት ስርዓተ-ትምህርት አኩሪ ተግባር መሆኑን አስገንዝበው በውይይቱ ገንቢ ሀሳቦች ተነስተው ወደፊት ለሚከፈተው ትምህርት ክፍል ግብዓት እንደሚኝ ገልፀዋል፡፡

የሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ ዲን ዶ/ር ሰፋ መካ በበኩላቸው በአውደ-ጥናት ውይይቱ በፋኩልቲው ሊከፈት ለታሰበው የሐይማኖቶች ጥናት ስርዓተ-ትምህርት ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች እንደሚመነጩ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ሰፋ በማስከተልም የሐይማኖቶች ጥናት ትኩረት ከሚሰጣቸው የአካዳሚክ ጉዳዮች አንዱ መሆኑንና ከአሁን በፊት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ወደ ስራ እንደተገባ ጠቁመው ፋኩልቲው የግዕዝ ትምህርት ክፍል በማቋቋም ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆናቸውን አውስተው በቅርቡ ሊከፈት ዝግጅቱን ያጠናቀቀው የሐይማኖቶች ጥናት ትምህርት ክፍልም ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም እንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡

የአውደ ጥናቱን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት ዶ/ር ተካልኝ ነጋ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ለሐይማኖቶች ትኩረት ሰጥቶ አውደ ጥናቱን ማካሄዱና ሊከፍት ያሰበው የሐይማኖቶች ጥናት ት/ክፍል ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡ በመድረኩም የሀይማኖት ጥናት ሲታሰብ ልማዳዊ ሃይማኖቶችንም ያከተተ መሆን እንዳለበት እና የአጠናን ዘዴውም ከተለመዱት የአጠናን ዘዴዎች የተለየ እና ጉዳዩን በትክክል መረዳት የሚያስችል መሆን እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

ዶ/ር ተካልኝ አክለውም በአገር አቀፍ ደረጃ በህገ-መንግስት ተግዳሮት ምክንያት የሐይማኖቶች ጥናት ትኩረት ሳይሰጠው ድፍን ሶስት አስርተ-ዓመታት ማለፉን ገልፀው በተናጠል ሳይሆን ሁሉንም ሐይማኖቶች ማጥናት ተገቢ መሆኑን በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

በአውደ-ጥናቱ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ተካልኝ ነጋ፣ ዶ/ር እንድሪስ መሐመድ፣ ዶ/ር ሰጥአርገው ቀናውና ዶ/ር ዘላለም ተፈራ ናቸው፡፡ ውይይቱን የመሩት ደግሞ ዶ/ር አደም ጫኔና ዶ/ር አንተነህ አወቀ ሲሆኑ በቀረቡት ገለፃዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምሁራን፤ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ-BDU

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ

Wisdom at the source of Blue Nile

Thank you for Inviting, like, share & visiting BDU page!

ለተጨማሪ መረጃዎች፡-

Telegram t.me/BDU_ISC_Official

Facebook: - https://www.facebook.com/bduethiopia

YouTube www.youtube.com/c/BduEduEt

LinkedIn www.linkedin.com/school/bahir-dar-university

Twitter: - https://twitter.com/bdueduet

Tiktok:- https://vm.tiktok.com/ZMLgRxdfL

website :- www.bdu.edu.et

 

 

Share