Outreach News

 

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ማበልፀጊያ ማዕከል (STEM Center) በየዓመቱ የሚያካሂደውን የልጃገረዶች የሳይንስ ካምፕ(STEM Girls Camp) ስልጠናና ውድድር በፔዳ ግቢ ለ8 ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ ለአሸናፊዎች የተለያዩ ሽልማቶችን በማበርከት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

በመዝጊያ ፕሮግራሙም የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ ም/ፕሬዘዳንት እና በአሁኑ ስአት ደግሞ የአብክመ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበን እና የከተማውን የትምህርት መምሪያ ም/ኃላፊ አቶ መላክ ጀመረን ጨምሮ  የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮምኒኬሽን ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተገኝተዋል፡፡

ዶ/ር ዘውዱ እምሩ በእግር ኳስ ጨዋታው ላሸነፉት ለፕሮፌሰር የአለምፀሀይና ለፕሮፌሰር ሶስና ቡድኖች ዋንጫ ከአበረከቱ በኋላ በመልዕክታቸው ተማሪዎች ወደ መጡበት ት/ቤት ሲመለሱ የቀሰሙትን እውቀት ለሌሎች የትምህርት አጋሮቻቸው እንዲያካፍሉና በያዙት ላይ ተጨማሪ እውቀት በመገብየት ለሞዴልነት የተጠቀሱትን ታዋቂ ሴት ሳይንቲስቶች በመተካት አገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው በአጠቃላይ ቆይታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡት ለዶ/ር ደብረወርቅ ቡድኖች የአንደኝነትን ማዕረግ የሚገልፀውን ዋንጫ አበርክተው በተማሪዎች መካከል የሚደረገው ፉክክር የወደፊት ታላቅነታቸውን እንደሚያሳይና ሳይንቲስቶችን እንደሚተኩ የሚያመላክት ነገር እንዳለ ጠቁመው ዕቅድ፣ጠንክሮ መስራትና ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በቁርጠኝነት መታገል ለከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደርስ አስገንዝበዋል፡፡

አቶ መላክ የምስክር ወረቀት ለቡድን ተወካዮች ከሰጡ በኋላ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው እያበረከተ ያለውን ጉልህ አስተዋፅኦ አመስግነው ለወደፊቱም ድጋፉና ክትትሉ እንዳይለይ በማሳሰብ ቢሮአቸው ይህን የመሰሉ ትውልድ የመቅረፅ ስራዎች ላይ በጋራ የመስራት እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በተማሪዎች መካከል የእግር ኳስ እና የዱላ ቅብብል ጨዋታ ውድድር፣ስነ ፅሁፍና የቆይታ ሪፖርት ቀርቦ የምስክር ወረቀትና ለአሸናፊ ቡድኖች የዋንጫ ሽልማት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡

ተማሪዎች ፕሮግራሙ እጅግ በጣም ጥሩ መሆኑን ገልፀው ለሌሎች እድሉን ላላገኙት የክፍል ጓደኞቻቸው ተደራሽነቱ እንዲሰፋ እንዲሁም ቀጣይነት እንዲኖረው በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

የብር አዳማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

ትዕግስት ዳዊት 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢን/ስት/ኮም ም/ፕረዚደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መንግሥት ባወጣው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650 ለዩኒቨርስቲዎች ከተሰጣቸው ሦስት ተልዕኮዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት በተለያየ ደረጃ እየተገበረ ይገኛል፡፡ ይህ በእለቱ የተከናወነው የትምህርት ቤት ስራ ምረቃም የዙህ ጥረት አንድ አካል እንደሆነ ዶ/ር ዘውዱ ገልፀው ይህን መሰል ስራዎችም ሞዴል መደረግ በሚችሉበት ደረጃ እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ዘውዱ አክለውም ለትምህርት ቤቱ ግንባታ እውን እንዲሆን ከተለያዩ ባለሙያዎች እና የመንግስት ኃላፊዎች ትብብር ባሻገር ኤፍጂሲኤፍ (FGCF) የተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅት ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡ ይህም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም. ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጋር በትምህርት ዘርፍ በትብብር ለመስራት ላደረጉት ስምምነት ተግባራዊ ማሳያ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የኤፍጂሲኤፍ (FGCF) አማራ ክልል አስተባባሪ አቶ አቢወት አሸናፊ የተገነቡትን 16 መማሪያ ክፍሎች፣ አንድ አስተዳደር ሕንፃ ፣ አንድ ቤተ-ሙከራ እና አንድ ቤተ-መጻሕፍት በምረቃ መርሃግብሩ ለተገኙት አካላት ያስጎበኙ ሲሆን የህንጻውን ክፍሎች እንዲሁም ውስጣቸው ስላሉት ቁሳቁሶች እና ስለሚሰጡት አገልግሎቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አቢወት በቀጣይ ደግሞ በዋነኛነት የትምህርት ቤቱን ምድረ-ግቢ ማሳመር፣ ለመምህራን የተለያዩ አቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት እንዲሁም ለተማሪዎች የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እንደታቀደ ገልፀዋል፡፡ የግንባታውን ወጪ ሶስት አካላት የሸፈኑት ሲሆን ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ 30%፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ወረዳው 40%፣ እንዲሁም ኤፍጂሲኤፍ (FGCF) 30%ቱን አዋጥተዋል፡፡ በትምህር ቤቱ ምርቃት ላይ የተገኙት የቋሪት ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ የፀዳው አጥናፍ እንደተናገሩት ወረዳው በትምህርት ጥራት በኩል ሰፊ ችግር ያለበት በመሆኑ ይህ ግንባታ ሲገነባ ሰፊውን ችግር ለማቃለል የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች ከፈራረሰ ትምህርት ቤት ወጥተው ደረጃውን በጠበቀ ህንጻ እንዲማሩ በመደረጋቸው የትምህርት ጥራት እንደሚሻሻል ጠቁመው የተገነባውን ህንጻ ማህበረሰቡ እንደራሱ እንዲንከባከበው አሳስበው ለዚህ ህንጻ መገንባት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት የአክብሮት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በመርሃግብሩ የተገኙት የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ በ1972 ዓ.ም የተገነባ እንደነበረ ጠቁመው አሁን ላይ አገልግሎት ለመስጠት የማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ እያለ አዲሱ ህንጻ መገንባቱ ከሃሳብ እና ጭንቀት እንደታደገቸው ገልጸዋል፡፡ አክለውም አሁንም ያልተሟሉላቸው እነደ ውሀ እና መብራት ያሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸው ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ወላጆች ልጆቻቸውን በርትተው እንደሚያስተምሩ ተናግረው ት/ቤቱን ወደ ሁለተኛ ደረጃ እንደሚያሳድጉትም ቃል ገብተዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሲቪልና የውሀ ምህንድስና ፋኩሊቲ 2ኛውን የአማራ ክልል የግብርና ፎረም “Small Scall Irrigation and Agricultural Technologies for Sustainable Development in Amhara Region” በሚል ርዕሰ ጥር 8/2010 ዓ/ም በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።

በዚህ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል አነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማትና አቅም ግንባታ ድጋፍ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ማማሩ ጽድቁ ናቸው። እንደርሳቸው ገለጻ ይህ ፎረም የተቋቋመው በአማራ ክልል አነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማት ላይ የሚታዩ የአቅም ክፍተቶችን ለማስወገድ፣ በግብርናው መስክ ላይ ሊኖሩ የሚችሉ እንከኖችን ለመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ በክልሉ ላይ ምርትን ለመጨመር እንዲሁም ሞዴል የሰርቶ ማሳያ ቦታዎችን በማቋቋም የግብርና ሰርቶ ማሳያዎችን በመስራት ለማሳየትና በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው መንግስታዊ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት በጋራ ተናበው እንዲሰሩ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። በአማራ ክልል በመስኖ ልማት ላይ በተለይም መስኖና ኢነርጂ፣ ግብርና ቢሮ፣ አውስኮድ፣ አመልድ፣ የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር እንዲሁም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ እንደሆነና በተለይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከኖርዌይ መንግስት ጋር በመተባበር በክልሉ ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎች ሲያካሂድ እንደቆየና ፎረሙም ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነና 2ኛውን የአማራ ክልል የግብርና ፎረም እንዳዘጋጀ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል በተፈጥሮ ሀብት የታደለና በተለይም ለግብርና ስራ አመች እንደሆነ የገለጹት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዜና ማርቆስ ባንቴ ናቸው። አክለውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በክልሉ ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎች እየሰራ እንደሆነና በመስኖ ልማት እንዲሁም አነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማት ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሆነና በተለይም በክልሉ ላይ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ምርምር በማካሄድ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው በዚህ ጉባኤ ላይም በክልሉ ውስጥ አነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማት ስራዎች እንዴት መሰራት እንዳለበትና በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና በአነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማት ስራዎች ላይ የራሱን ድጋፍ እንደሚያደርግና በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ግብርና የግብርና ባለሙያዎችን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ሳይሆን የተለያዩ የሙያ መስኮችን የሚመለከትና የሚዳስስ ጉዳ እንደሆነ የተናገሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሲቪልና የውሀ ምህንድስና መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፎረሙ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ ናቸው። አክለውም በዚህ ፎረም ላይ ለአርሶ አደሮች የሚጠቅሙ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ብሎ በመለየትና የክልሉን ህዝብ የሚጠቅሙ ስራዎችን ለመስራትና ምን እየተካሄደ ነው? ምን አይነት ጥረቶች አሉ? ማን ማን ጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው? ምን አይነት ሀሳቦች አሉ? የሚለውን ለመገንዘብ እና ፖሊሲ አውጭዎችና አስተግባሪዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አጋር አካላት ከዚህ ውይይት ላይ ግንዛቤ በመውሰድ እንዲሰሩና የጋራ ግንኙነታቸውን እንዲያሰፉ ለማድረግ እንደሚያግዝም አስተባባሪው ተናግረዋል።

በBDU-NORHED ኘሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪነት በትምህርትና ስነ ባሕርይ ኮሌጅ ፣ በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ማልፀጊያ ማዕከል አና በFGCF ትብብር ከአማራ ክልል አራት ዞኖች (ምዕራብ ጎጃም፣ምስራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር እና አዊ) ከሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ 100 መምህራን የዘጠኝ ቀናት ስልጠና ተሰጠ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፔዳጐጅና ትምህርት ምርምር ተቋም ዳይሬክተርና የBDU-NORHED ኘሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ዳዊት አስራት ስልጠናው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በተለይም የሳይንስና የሂሣብ ትምህርቶች ላይ ተማሪዎች ፅንሰ ሀሣቦችን በቀላሉ እንዲገነዘቡ ለማድረግ የሚረዱ መንገዶችን ማስተማርን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የእያንዳንዱ ባለሙያ ግዴታ መሆኑና የዚህ እንቅስቃሴ አንድ አካል ሊሆን የሚችለው ደግሞ የመምህራንን አቅም ማጎልበት እንደሆነ ዶ/ር ዳዊት ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ዳዊት አክለውም የአጭር ጊዜ ስልጠናው ትኩረት ያደረገው በአምስት ጉዳዮች ማለትም በሂሳብ እና ሳይንስ ትምህርት ስነ-ዘዴ፣ በተግባራዊ ምርምር፣ ስርዓተ-ፆታን መዕከል ያደረገ የማስተማር ዘዴ እና በልይይት ማስተማር እና ምዘና ላይ ነው ብለዋል፡፡

በስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ መምህራን ስልጠናው ከዕለት ተዕለት የማስተማር ስራቸው ጋር በቀጥታ የሚገናኙና በቀላልና ከአካባቢ የሚገኙ ቁሳቁሶችን ተጠቅመው በሚሰሯቸው ሙከራዎች ተማሪዎች የሳይንስና የሂሳብ ፅንሰ ሃሳቦችን በቀላሉ ለመገንዘብ እንዲችሉ የሚያግዙ መንገዶችን የተማሩበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን ወክለው በስልጠናው የተገኙት አቶ ልሳነወርቅ ፋንታሁን ዩኒቨርስቲው ተነሳሽነቱን ወስዶ ስልጠናውን መስጠቱን አመስግነው ሰልጣኞችም በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በስራ ላይ በማዋል ለትምህርት ጥራት መሻሻል የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበው የክልሉ ትምህርት ቢሮውም በመሰል ጉዳዮች ላይ ወደፊት ከዩኒቨርስቲው ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ኘሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ሙላው አበበ ለስልጠናው ተሳታፊዎች ሰርተፊኬት የሰጡ ሲሆን ዶ/ር ሙሉነሽ በመዝጊያ ንግግራቸው የሁሉም ሙያ መነሻው መምህርነት ትልቅ ፀጋ መሆኑን ገልፀው ሰልጣኝች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን እዉቀት ወደ መሬት አውርደው ተግባራዊ እንዲያደርጉት አሳስበዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ለተቋሙ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ሰኔ 15 እና 16 2009 ዓ.ም የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ ስልጠና በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ሰጠ፡፡ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ዋና ዓላማው አድርጐ እየሰራ ያለው መማር ማስተማር፣ ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት እንደሆነ እና ይህ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ስልጠናም የማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ አካል መሆኑን እና ስልጠናው አዳጋ ሲደርስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የሚከሰት ጉዳትን መቀነስ እንዲቻል ታስቦ የተሰጠ እንደሆነ የተቋም መምህርና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ታረቀኝ አያሌው ገልፀዋል፡፡ ​አስተባባሪው አክለውም በዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከውጭ ማህበረሰብ ዘንድ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ እንዴት እንደሚሰጥ ግንዛቤ ባለመኖሩ የተለያዩ ችግሮች እንደሚፈጠሩ እና ክብር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ለህልፈተ ሞት እንደሚዳረግ ገልፀው ስልጠናው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የመጡ ተማሪዎች ጨምሮ ያካተተ በመሆኑ ከራሳቸው አልፎ ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያግዝና በቀላሉ ተደራሽ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ሰልጣኞችም የተሰጣቸውን ስልጠና ወደ ተግባር ከመቀየር ባሻገር ለማህበረሰቡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንዲሰሩ አስተባባሪው ጨምረው አሳስበዋል፡፡ በአደጋ ጊዜ የሚከሰት ሞትን በመጀመሪያ እርዳታ ህክምና ከ 40 እስከ 60% መቀነስ እንደሚቻል ነገር ግን ይህ ግንዛቤ በሀገራችን አደጋ በሚከሰትበት ቦታ በፍጥነት የሚገኙትን የመከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ አካላት ጨምሮ ዝቅተኛ እንደሆነ በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም መምህር እና የስልጠናው ተሳታፊ አቶ አለበል አይናለም ገልፀዋል፡፡ አቶ አለበል አክለውም የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ለመስጠት ትምህርቱን ብቻ መማር በቂ እንዳልሆነ እና ከውስጥ የሚመነጭ ፍላጐት እንዲሁም በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ጠቁመው የትምህርት ክፍሉ ወደፊት ከዩኒቨርሲቲው እና ከአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም ከቀይ መስቀል ጋር በመሆን ግንዛቤ ለመፍጠር መሰራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ከአፍሪካ ሀገሮች የተሻለ ደረጃ ላይ ብትገኝም በእንስሳት መኖ እጥረት ምክንያት ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ችግር አኳያ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት የተለያዩ የንጥረ ነገር ውህዶችን በመጠቀም የፅንሰ-ሃሳብና የተግባር ስልጠና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በግብርናና አካባቢ ሣይንስ ኮሌጅ ግቢ ቤተ-ሙከራ ለ7 ተከታታይ ቀናት ሰጥቷል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር የሻምበል መኩሪያው ቴክኖሎጅን በመጠቀም ማንኛውም ማህበረሰብ በቀላሉ አረንጓዴ የእንስሳት መኖ በአጭር ጊዜ፣ በአነስተኛ ጉልበትና ውሃ በርካታ የእንስሳት መኖ በማዘጋጀት መጠቀም የሚቻልበትን ዘዴ ለማሳወቅ ስልጠናው ፈር ቀዳጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለቴክኖሎጂው ዋና ግብዓት የሆነውን ውህድ በዩኒቨርሲቲው የኬሚስትሪ ት/ክፍል ሙሁራን ተሰርቶ የቀረበ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከGIZ የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የመጡት አሰልጣኝ አቶ ኃይለየሱስ አባተ የቴክኖሎጂውን ግኝትና አዋጭነት ሲገለፁ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው፣ በተለይ ዝናብ አጠርና ድርቅ በሚያጠቃቸው ቦታዎች አካባቢ በስፋት መሰራት እንደሚቻል፣ በ7 ቀናት ውስጥ ከ25-30 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አረንጓዴ መኖ ማድረስ እንደሚቻል እንዲሁም ከ 1 ኪሎ ግራም ገብስ ከ6-10 ኪሎ ግራም የሚመዝን የእንስሳት መኖ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ አያይዘውም መኖው በተለይ ለእንቁላል ጣይ ዶሮዎች የንጥረ ነገሩ ውህድ ከፍተኛ ፕሮቲን ስላለው በርካታ እንቁላል የመጣል አቅማቸውን እንደሚያጐለብትና ስልጠናው ከሙከራ እስከ ትግበራ መሰጠቱን አስገንዝበዋል፡፡ ሰልጣኞች በባሕር ደር ከተማ የተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ የኮሌጁ የእንስሳት እርባታ ሠራተኞች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን መምህራንና የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ሲሆኑ ከስልጠናው ከፍተኛ ግንዛቤ እንደጨበጡና በቆይታቸው መኖው ለእንስሳት መቅረብ መቻሉን ብሎም የኮሌጁ ላሞችና በጐች ሲመገቡት ማስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢኮ-ቱሪዝም እና ብዝሃ-ህይወት ጥበቃ ማህበር ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቤዛዊት ቤተ መንግስት የወፍ ቆሎ (ሣንታና ካማራ) የተሰኘውን መጤ አረም ማስወገድና መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ለማስጀመር የግማሽ ቀን አውደ-ጥናት በቤንማስ ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡
ማህበሩ የኢትዮጵያ በጐ አድራጐት ማህበር ሆኖ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በርካታ አኩሪ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ለማህበሩ በሰጠው 25 ሄክታር የሚሊኒየም ፓርክ ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የወፍ ቆሎ (ሣንታና ካማራ) የተሰኘውን መጤ አረም  ለማስወገድና መልሶ ለማልማት አውደ-ጥናቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ከእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው ጋር ያስተላለፉት የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አያሌው ወንዴ  ናቸው፡፡
የፕሮግራሙን የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ ጥሪውን አክብረው ለመጡት ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውንና ፕሮግራሙን ላዘጋጀው አካል ምስጋና አቅርበው ዩኒቨርሲቲው ከአሁን በፊት የተለያዩ መጤ አረሞችን በማጥፋት ዘመቻ በስፋት ሲሳተፍ እንደቆየ ገልፀው የወፍ ቆሎን (ሣንታና ካማራ) የተሰኘውን መጤ አረም ለማጥፋትና በሌላ አገር በቀል ዛፎች በማልማት ፓርኩ የምርምር ማዕከልና የሚጐበኝ ማራኪ ቦታ ይሆን ዘንድ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል፡፡ ም/ፕሬዚዳንቷ አያይዘውም በፅንሰ ሀሳብ የቀረበው ወደ ተግባር እንዲቀየርና ፓርኩን የማልማት ሥራው እንዲጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለበት በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሙህራንና የማህበሩ አባላት ሲሆኑ 80% የሚሆኑ አባላት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች እንደሆኑ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ለማህበሩ መመስረትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከገንዘብ ድጋፍ ጀምሮ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዝታ የኔአለም ተናግረዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ለወደፊት ፖርኩ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መስፋፋትና መጠናከር እንዳለበት ከቤቱ ተጠቁሞ የቀረቡት ፅሁፎች የመነሻ ሀሳብ እንደሆኑና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የቤት ሥራ አድርጐ እንዲወስደው ብሎም በእኔ ባይነት ስሜት ማህበሩ እንዲስፋፋ ከታዳሚዎች ሀሳብ ተሰንዝራል፡፡ 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በግልገል አባይ ወንዝ መግቢያ ያሉ ውሃ አዘል መሬቶች ማገገምና ዘላቂ ልማት ኘሮጀክት (Rehabilitation and Sustainable Utilization of little Abay River Mouth Wetlands Project) በወንዙ ተፋሰስ ዙሪያ ያከናወናቸውን ስራዎች አስመልክቶ የአንድ ቀን ጉብኝት አካሄዷል፡፡
ኘሮጀክቱ ከተጀመረ  ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን የአካባቢውን ውሃ አዘል መሬት መሪ እቅድ ማውጣት፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ፤ በተለይ ለተማዎች እና ለተመራማሪዎች እንዲሁም ለአርሶ አደሮች፣ የደንገልን ተከላና እንክብዛቤ ማስፈን፣ የብዝሀ ህይወት ሀብት የሆነውን ጣና ሀይቅን መጠበቅ ዋና ዋና ዓላማዎች እንደሆኑ የኘሮጀክቱን በዋናነት የያዙት ሶስት የዩኒቨርሲቲው ሙህራን/ ዶ/ር ምንውየለት መንግስት፣ ዶ/ር ዋሴ አንተነህ እና ዶ/ር አማረ ሰውነት/ ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህ አላማዎች መካከል ከ85-90 % የሚደርሱት የተከናወኑ እንደሆኑና ከዛም በዘለለ የአካባቢውን ስራ አጥ ወጣት በማደራጀት በአሳ ማስገር ሥራ ተሰማርተው እራሳቸውን እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በአባይ ተፋሰስ አካባቢ ከ4500 ሕዝብ በላይ የሚኖርባቸው ሁለቱ ቀበሌዎችን ማለትም ከሰሜን አቸፈር ወረዳ እስቱሚት ቀበሌ እና ከባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ልጆሚ ቀበሌ በተሻለ ዘዴ ኑሮአቸውን እንዲመሩ ለማስቻል ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የፕሮጀክቱ ባለቤቶች ገልፀዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ኘሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ የተገኙ ሲሆን ከጉብኘቱ በርካታ ያልጠበቋቸው ነገሮች ተሰርተው እንዳገኙ እንዲሁም ለወደፊቱ በደለል በመሞላት ምክንያት ተጎጅ የሆነ ያለውን የጣና ሀይቅ ለመታደግ ሁሉም እርብርብ ማድረግ እንዳለበት ገልፀው በኘሮጀክቱ አማካኝነት የተገኙትን ሁለት የሞተር ጀልባዎች ለስቱሚቱ እና ለልጆሚ ቀበሌ አስተዳደሮች አስረክበዋል፡፡ “የ CEPF(Eastern Afromontane Regional implementation Team” ) አማካሪ  የሆኑትን አቶ አብዱራሀማን ኩብሳን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ፣ ሙህራንና የአካባቢው ማህበረሰብ በጉብኝቱ ተሳትፈዋል፡፡ 

Arresting Gullies (ምርኮኛው ቦረቦር), a documentary film by the Faculty of Civil and Water Resources Engineering, BiT.

Click this link to watch...https://www.youtube.com/watch?v=Z4LhmAdjh0U&feature=youtu.be

The office of Vice president for Research and Community Services has disclosed video reports showing the major activities of research and community services carried out in 2006 & 2007 E.C. academic year.

Click the following links to watch the details...
https://www.youtube.com/watch?v=ENpL9A7FYhk
https://www.youtube.com/watch?v=Z9lPlUhnpHs&feature=youtu.be
https://www.youtube.com/watch?v=YPCF-6TD41o&feature=youtu.be

Pages