ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የአጭር ጊዜ ስልጠና ተሰጠ

በBDU-NORHED ኘሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪነት በትምህርትና ስነ ባሕርይ ኮሌጅ ፣ በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ማልፀጊያ ማዕከል አና በFGCF ትብብር ከአማራ ክልል አራት ዞኖች (ምዕራብ ጎጃም፣ምስራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር እና አዊ) ከሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ 100 መምህራን የዘጠኝ ቀናት ስልጠና ተሰጠ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፔዳጐጅና ትምህርት ምርምር ተቋም ዳይሬክተርና የBDU-NORHED ኘሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ዳዊት አስራት ስልጠናው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በተለይም የሳይንስና የሂሣብ ትምህርቶች ላይ ተማሪዎች ፅንሰ ሀሣቦችን በቀላሉ እንዲገነዘቡ ለማድረግ የሚረዱ መንገዶችን ማስተማርን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የእያንዳንዱ ባለሙያ ግዴታ መሆኑና የዚህ እንቅስቃሴ አንድ አካል ሊሆን የሚችለው ደግሞ የመምህራንን አቅም ማጎልበት እንደሆነ ዶ/ር ዳዊት ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ዳዊት አክለውም የአጭር ጊዜ ስልጠናው ትኩረት ያደረገው በአምስት ጉዳዮች ማለትም በሂሳብ እና ሳይንስ ትምህርት ስነ-ዘዴ፣ በተግባራዊ ምርምር፣ ስርዓተ-ፆታን መዕከል ያደረገ የማስተማር ዘዴ እና በልይይት ማስተማር እና ምዘና ላይ ነው ብለዋል፡፡

በስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ መምህራን ስልጠናው ከዕለት ተዕለት የማስተማር ስራቸው ጋር በቀጥታ የሚገናኙና በቀላልና ከአካባቢ የሚገኙ ቁሳቁሶችን ተጠቅመው በሚሰሯቸው ሙከራዎች ተማሪዎች የሳይንስና የሂሳብ ፅንሰ ሃሳቦችን በቀላሉ ለመገንዘብ እንዲችሉ የሚያግዙ መንገዶችን የተማሩበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን ወክለው በስልጠናው የተገኙት አቶ ልሳነወርቅ ፋንታሁን ዩኒቨርስቲው ተነሳሽነቱን ወስዶ ስልጠናውን መስጠቱን አመስግነው ሰልጣኞችም በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በስራ ላይ በማዋል ለትምህርት ጥራት መሻሻል የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበው የክልሉ ትምህርት ቢሮውም በመሰል ጉዳዮች ላይ ወደፊት ከዩኒቨርስቲው ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ኘሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ሙላው አበበ ለስልጠናው ተሳታፊዎች ሰርተፊኬት የሰጡ ሲሆን ዶ/ር ሙሉነሽ በመዝጊያ ንግግራቸው የሁሉም ሙያ መነሻው መምህርነት ትልቅ ፀጋ መሆኑን ገልፀው ሰልጣኝች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን እዉቀት ወደ መሬት አውርደው ተግባራዊ እንዲያደርጉት አሳስበዋል፡፡