የ ISSD/ክልላዊ አውደጥናት

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት /ISSD/ ክልላዊ አውደጥናት አካሄደ!!

=======================================================
 

በሙሉጌታ፡ዘለቀ
የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማትፕሮጀክት /ISSD/ እስካሁን የመጣበትን የስራ ዘመን ለመገምገምና በቀጣይነቱ ላይም ለመምከር በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋራ ውይይቱን በባህር ዳር ከተማ አካሄደ፡፡

ዶ/ር ደረጀ አያሌው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት /ISSD/ ዋና ዳይሬክተር (ISSD Project Coordinator) በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የአውደ ጥናቱ ዋና አላማ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን ለመገምገምና ፕሮጀክቱ ከስድስት ወር በኋላ የስራ ጊዜውን የሚያበቃበት ወቅት በመሆኑ ይህ ፕሮጀክት ሲሰራቸው የነበሩትን ስራዎች በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት እና የፕሮጀክቱ የቅርብ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንዳሉት የሀገራችንን የግብርና ምርትን ውጤታማ ለማድረግ ከበሽታ የነፃና በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት ሊሰጥ የሚችል ምርጥ ዘር ወሳኝ መሆኑን ተናግረው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በየጊዜው በዚህ ዘርፍ ከሚሰሩ ፕሮጀክቶች ጋር ከሚያደርገው ግንኙነቶች ውስጥ አንዱ የISSD ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ፕሮጅክት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ግንዛቤን ከፍ ያደረገና ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎችን ያመጣ ብሎም የተገበረ እንዲሁም በቀጣይነቱ ዙሪያ እየሰራ ያለ እንደሆነ  ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግዙፍ ተቋም እንደመሆኑ ISSD Project እስካሁን የሰራቸውን ስራዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ፈጠራና ምርጥ ዘርን የማዳረስ ስራን በስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ይህ ጉባኤ ለወደፊቱ በምርጥ ዘር ላይ ቋሚ ስራ ለመስራት በምን መልኩ መሄድ እንደሚገባ መክሮ የተጀመሩ ስራዎችን ከግብ ማድረስ እንደሚገባ በአፅኖት ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የስራ ጊዜው ቢጠናቀቅ እንኳን የአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ዩኒቨርሲቲዎቸ /እና አጋር ተቋማት ይህንን በጎ ስራ ማስቀጠል እና አርሶ አደሩን የተለያዮ ስልጠናዎችን በመስጠትም ሆነ ምርጥ ዘር በማቅረብ መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የISSD ፕሮጀክት የእሴት ሰንሰለት ባለሙያ የሆኑት አቶ መስፍን አስታጥቄ  ለጉባኤው ተሳታፊ እንዳሉት ባሳለፍነው አስር ዓመት በዋናነት የተመረጠና በምርምር የተገኘ ጥራት ያለው  ዘርን ወቅቱን ጠብቆ በተፈለገው መጠን ለአርሶ አደሩ እንዲደርስና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘዬ ለመቀየር እንዲሁም ኢኮኖሚን ለማሳደግ አልሞ መስራቱን ተናግረዋል። የፕሮጀክቱን የአስር አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርትም አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም በፕሮጀክቱ  የተገኙ ጠንካራና ደካማ ጐኖችን በማንሳት ውይይት የተደረገ ሲሆን ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም ተሳታፊዎቸ አስቀምጠዋል፡፡  ይህንን ፕሮጀክት የማስቀጠል ስራ የዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን የሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም እንደሆነ ተገልጿል፡፡  በውይይቱ ላይ  የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በተለያ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ ቢሮዎች የተጋበዙ እንግዶች እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚደንትን ጨምሮ ዳይሬክተሮች እና ሌሎች ምሁራን ተገኝተዋል፡: