Latest News

                     የተሻሻለ ሰብል ዝርያ በሰርቶ ማሳያ የመስክ ምልከታ ተደረገ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት በታች ጋይንት ወረዳ ቆጥ መንደር የተሻሻለ የስንዴና ገብስ ዝርያ ሰርቶ ማሳያ ላይ የመስክ ላይ ጉብኝትና ምክክር መስከረም 26 አደረገ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት ማኔጀር የሆኑት ዶ/ር አልማዝ ጊዜው በመድረኩ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ እየሰራ ያለው CASCAPE እና ISSD ከተሰኙ ፕሮግራሞች የተገኙ ምርጥ የግብርና ተሞክሮዎችን የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ 10 የፕሮግራሙ ወረዳዎች ላይ ማስፋት ነው፡፡ ለዚህም ውጤታማነት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር የሶስት ዓመት ፕሮግራም ምርጥ ተሞክሮዎችን በማላመድ፣ በማረጋገጥ እና በማስፋት የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ የድርጅቶችንና የተቋማትን አቅም ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት በደቡብ ጎንደር ጋይንት ወረዳ ቆጥ መንደር ቀበሌ ታይ የተሰኘ የስንዴ እና ትራቪለር የሚባል የቢራ ገብስ ዝርያ የማሳ ላይ ሰርቶ ማሳያ እና የቅድመ ማስፋፋት ስራዎች እንደተሰራ ተናግረዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተግባር ተቀብለው እየሰሩ ያሉ አርሶ አደሮች እንዳሉት የቀረበላቸው ዝርያ እስካሁን ከተመለከቱት የተሻለ መሆኑን ተናግረው ለመኖ የሚሰጠው ውጤት አናሳ በመሆኑ ቢሻሻል በማለት አሁንም የግብዓትና የማማከር ድጋፋቸውም ከዚህ በላቀ መልኩ እንዲቀጥል አሳስበዋል ፡፡ ከዚህ ባሻገር በመስክ ምልከታው በታዩ ጠንካራ ጎኖችና ጉድለቶች ላይ ከወረዳ እስከ ክልል ከሚገኙ የፕሮጀክቱ አጋር አካላት ጋር የአካባቢው አርሶ አደሮች በተገኙበት ምክክር ተደርጓል፡፡ በምክክሩም ላይ ከአርሶ አደሮች እና ከግብርና ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንዳሉት 2011-ለ2012 በጀት አመት በተሠሩ የግብርና የተግባር ስራዎች ላይ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በግልፅ ተመልክቶ ደካማውን ደካማ ጠንካራውን ጠንካራ ለማለት እና አዳዲስ አሰራር ፣ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ፤ ከቀበሌ ቀበሌ ፣ ከአርሶ አደር ወደ አርሶ አደር ለማስፋፋትና ለአካባቢው ተስማሚ የሚሆነውን ዝርያ ለመምረጥ የመስክ ምልከታው ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡

 

በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር ምክክር ተደረገ !!

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች አቀባበል በማድረግ ዙሪያ ከዘጠኝ በላይ ከሚሆኑ የባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር በዩኒቨርሲቲው የጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ምክክር አደረጉ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮምንኬሽ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንዲሁም የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የባህር ዳር ወጣቶች በዩኒቨርሲቲው ፀጥታ ጉዳይና የተማሪዎችን ደንነት ከመጠበቅ አንፃር እያበረከቱት ያለውን አስተዋፆ አድንቀዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲውም የስራ እድሎችን በመፍጠርና የወጣቶችን አቅም በመገንባት የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ ጠቁመው ወጣቶችም የባሕር ዳር ከተማና  የዩኒቨርሲቲው ስም በበጎ እዲነሳ አሁንም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት የነበረውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል፡፡

ከባሕር ዳር ከተማ የተወጣጡ የወጣት ማህበራት  ተወካዮች እንደገለጹት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሞባይልና የላፕቶፕ ዘረፋዎች የሚደርስባቸው ተብለው የተለዩ ዋና ዋና የሚባሉ መስመሮች የመንገድ መብራቶቻቸው የጠፉ እና አንዳንዶችም መስመር ሊዘረጋላቸው የሚገባ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ከመብራት ሀይል እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡  አክለውም ወጣቶቹ በባሕር ዳር ከተማም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ለተነሱት ጥያቄዎች በባሕር ዳር   ዩኒቨርሲቲ  ከፍተኛ አመራሮች መላሽ ተሰጥቷል፡፡    

                      በአደገኛ-ፅ ተጠቃሚነት ዙሪያ የምክክር አውደ ጥናት ተካሄደ

በወንዳለ ድረስ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከመቋሚያ የማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር መስከረም 20 በሴኔት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዩኒቨርሲቲን መሠረት ያደረገ የፀረ ሱስ ንቅናቄ ለማድረግ የአንድ ቀን አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ አዲስ ተማሪዎች በአንዳንድ በሱስ ተጠቂ ጓደኞቻቸው ምክንያት ወደ ሱስ የመግባት ችግር እንዳለ አውስተዋል ፡፡ ለዚህም ዶ/ር ተስፋዬ  እንዳሉት መምህራን፣ ሰራተኞችና ኃላፊዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመው የአካባቢው ማህበረሰብም ተማሪዎችን ሱስ የሚያሲዙ የንግድ ቦታዎችን ከመክፈት ቢቆጠቡ በሚል የምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ከአውደ ጥናቱም ጠንከር ያለ ተቋም የመፍጠርና ቀጣይነቱ ላይ መስራት ይጠበቃል ብለዋል ፡፡

በአውደ ጥናቱ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት የመቋሚያ ማህበረሰብ ልማት ማህበር መስራች እና ዋና ስራ አስኪሃጅ  አቶ ኤልያስ አላዩ ማህበሩ በሀረማያ፣ ሀዋሳና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች የፀረ ሱስ ንቅናቄ በማድረግ እስካሁን ከ600 በላይ ወጣቶችን ከሱስ መታደግ የቻለ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል በመንቀሳቀስ ከአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነትና  ሱሰኝነት ራሱን መጠበቅ የሚያስችል ቁመና ያለው ህብረተሰብ መፍጠር የመህበሩ አላማ መሆኑን ጠቁመው የአደገኛ-እፅ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት ዘር ፣ ቀለም ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣  ስራ፣ እድሜና የኑሮ ደረጃን ሳይለይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እንደሚያጠቃ ተናግረዋል፡፡ በጣም አስከፊ የሆነው የአደገኛ-እፅ ጥፋት፤ አምራች የሆነውን የኢኮኖሚ ክፍል ማለትም ወጣቱን በከፍተኛ ፍጥነት እየጨረሰ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ የሃይማኖት ተቋማትና የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡን ጨምሮ በከተማው የሚገኙ ተቋማት በመገኘት የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በሱስ የመጠመድ ሂደት ላይ ትኩረት ሰጥተው የተወያዩ ሲሆን በቀጣይም ተማሪዎች ከመግባታቸው በፊት ኮሚቴ በማቋቋም ጠንከር ያለ ስራ ለመስራት እቅድ ይዘዋል ፡፡

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሀገሪቱን ስፖርት ለማሳደግ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ መሆኑ ተነገረ !!

……………………………………………………………………………

 በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየተዳከመ የመጣውን የእግር ኳስ ስፖርትን ጨምሮ በአትሌቲክስ እና በሌሎችም የስፖርት አይነቶች ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች በሚል ምድብ ታዳጊዎችን  ለማሰልጠን ከሦስት ወር በፊት ለታዳጊዎች ይፋዊ ጥሪ አውጥቶ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ባሕር ዳር ከተማ ካሉ ትምህርት ቤቶት የተወጣጡ እና ተሰጥኦ ያለቸውን በርካታ ታዳጊዎችን በማሰባሰብ ማጣሪያ ሲያደርግ ቆይቶ በሁለቱ ምድብ የተመረጡ ከአንድ መቶ ሰባ ባለይ ታዳጊዎችን  በፕሮጀክት አቅፎ በዩኒቨርሲቲው የስፖርት አካዳሚ ሊያሰለጥናቸው እንደሆነ ተነገረ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በዝግጅቱ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ባስገነባው ሁለገብ የስፖርት አካዳሚ ክህሎት ያለቸው ታዳጊዎች በአካዳሚው የስፖርት መምህራን ታግዘው መሰልጠናቸው ምን አልባት አሁን እየተዳከመ የመጣውን የእግር ኳስ ስፖርት እንዲያንሰራራ የበኩሉን እነደሚያበረክት ገልፀው ለሀገርም ከፍተኛ ኩራት የሚሆኑ ስፖርተኞች ማፍራት እንደሚቻል እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ፍሬው አክለውም ይህ እውን የሚሆነው የታዳጊ ህፃናት ጥረት ሳይንሰዊ በሆነ ስልጠና ሲታገዝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህ ደግሞ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ መምህራን እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊውን የቁሳቁስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ለኢትዩጵያ የስፖርት የሚጠበቀውን ማበርከት እንደሚቻ ገልፀዋል፡፡

የአማራ ስፖርት ኮሚሽን የተሳትፎ ስልጠና ውድድር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ምትኩ አክሊሉ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እነዚህን ታዳጊዎች   እና ከ50 በላይ የሚሆኑ የአትሌቲክስ ሰልጣኞችን ለማሰልጠን  እየወሰደ ያለውን ኃላፊነት አድንቀው እየተዳከመ ያለውን ስፖርት ለመታግ ብሎም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋፃ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም በክልላችን ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን አርአያ በመከተል ለሀገራችን ስፖርት ማደግ የበኩላቸውን አስተዋፆ እንዲያደርጉ ጠቁመው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለሚያደርገው በጎ እንቅስቃሴ የአማራ ስፖርት ኮሚሽን ከጎኑ በመሆኑን አቶ ምትኩ ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዲን ዶ/ር ተስፋዬ ደሳለኝ በበኩላቸው ስልጠናው በእለቱ የተመለመሉትን ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችን  እና ከሦስት አመት በፊት በዩኒቨርሲቲው እገዛ እየሰለጠኑ ያሉትን ከ50 በላይ የሚሆኑ የአትሌቲክስ ሰልጣኞች በይፋ በዩኒቨርሲቲው ታቅፈው አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡

በእለቱ በባሕር ዳር ከተማ ለረጅም አመታት የሴቶችን የቅርጫት ኳስ ቡድን ሲደግፉ የነበሩት አቶ በለጠ ለሚያሰለጥኑት ቡድን የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ እውቅና በመስጠት የቁምጣና የማሊያ ሽልማት ተበርክቷል፡፡በመጨረሻም በፕሮጀክቱ  ለታቀፉ ለሁሉም ታዳጊ ህፃናት የቁምጣና  የማሊያ ሽልማት በባሕር ዳር ዩኒቨርርሲቲ ፕሬዚዳንት በዶ/ር ፍሬው ተገኘ እጅ ተረክበዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደን  ጨምሮ አሰልጣኝ መምህራን ከአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን የመጡ የሚመለከታቸው አካላት እና ሌሎች ተገኝተዋል፡፡  

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሰራተኞች በዩኒቨርሲቲው የ2011 ዓ.ም. ዕቅድ አፈፃፀምና የ2012 ዓ.ም. ዕቅድ ዙሪያ እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ የሳይንስ ኮሌጅ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እንዲሁም የማሪታይም አካዳሚና ዋናው ግቢ አስተዳደር ሰራተኞች ተሳታፊ ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችም ተገኝተዋል። የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሀኑ ገድፍ የዩኒቨርሲቲውን የ2011 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ በፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ፍሬው ተገኘ አወያይነት ሰራተኛው እየተወያየ ነው።ይህ ውይይት ከሌሎች ግቢዎች አስተዳደር ሰራተኞች ጋርም በመጪዎቹ ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።

የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ  በክልሉ የአርብቶ አደሮች የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስራ ላይ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡

 

የመምህራንን የቀድሞ ሙያና ክብር ለመመለስ መስራት እንደሚገባ ተነገረ!!

የመምህርነት ሙያን ማህበረሰባዊ እይታዎችን ለማሻሻል ሃገራዊ ንቅናቄ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ተካሄደ፡፡

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ  በሀገራችን መምህርነት እንደ ሙያ ጥያቄ ውስጥ እንደገባ የሚያሳዩ ጠቋሚዎች እንዳሉ ተናግረው እየተዳከመ ለመጣው የሙያዎች ሁሉ መሰረት ለሆነው መምህርነት ማህበረሰቡ፣ የመንግስት  ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች  አጋር አካላት ቀደም ሲል የነበረውን ክብርና ተቀባይነት ለመመለስ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ አሁን በሀገር ደረጃ  ያጋጠመው ችግር በአህጉርና በአለምአቀፍ ደረጃ የሚያጋጥም መሆኑን ገልፀው በንቅናቄ ብቻ ሳይሆን በችግሮች ላይ ተመርኩዞ የመፍትሄ ሀሳቦችን በመለየትና ተግባራዊነታቸውን በማረጋገጥ ችግሩን መቀነስ ብሎም ማጥፋት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡  

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ይሀን የተከበረ ሙያ በጥንካሬ እንዲወጣ ከመምህራን ምልመላ ጀምሮ ስልጠናዎችን በበቂ መልኩ መስጠትና መምህራንን ለሚያሰለጥኑ ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ ሙያውን በመሸሽ ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኙ የትምህርት መስኮችን የመቀላቀል ዝንባሌዎች እየበዙና እየጠነከሩ  መምጣታቸው የመምህርነት ሙያ አደጋ እንዲጋረጥበት አድርጓል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ተማሪው፣ ህብረተሰቡ፣ ፖለቲከኛው እና መንግስት ስለመምህራን ምን ይላሉ ከማለት ባለፈ መምህራን ስለራሳቸው ምን ይላሉ የሚለውን በአንክሮ መመልከት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ መምህራን የሙያው ፍቅር ሳይሆን የገንዘብ ክብርን እንደሚያስቀድሙ ይታወቃል ስለዚህ መጀመሪያ ለሙያው ተገዥ መሆን እንዳለባቸው ገልፀው ደመወዝ በመጨመር ብቻ ሙያው ጠንክሮ እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡና በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው የመምህርነት ተሞክሮዎቻቸውን ያቀረቡ መምህራንና የተማሪ ወላጅ ማህበር ተወካዮች ንግግር አድርገዋል፡፡ በዳንግላ ወረዳ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩትና በሀገራችን የበጎ ሰው እጩ ሽልማት ባለቤት የሆኑት መምህር ስዩም ቦጋለ የተሰብሳቢዎችን ቀልብ የያዘ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም መምህር ማለት ለራሱ የሚኖር ሳይሆን እራሱ እንደሻማ ቀልጦ ለተማሪዎቹ ብርሃን የሚሆንና ለተቸገሩ ተማሪዎች ከፈጣሪ በታች በበጎ ተግባር የሚደርስ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው ከደመዎዛቸው 75% በመቀነስ ለተቸገሩ ተማሪዎች እንደሚረዱና በተለያዩ ምክንያቶች ተማሪዎች ችግር ሲደርስባቸው ከጎናቸው በመሆን ሳይሰለቹ እንደሚረዷቸውና በዚህ መልኩ ያስተማሯቸው ተማሪዎች ጥሩ ውጤት በማምጣት ለሀገርና ለወገን ኩራት ሆነው ማየታቸውና በዚህ ስራቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተማሪ ወላጅ ማህበርን ወክለው ንግግር ያደረጉት ኢ/ር ጌታቸው ሰጠኝ እንዳሉት የመምህርነት ሙያ አሁንም ቢሆን እንዳልወደቀ ገልፀው ነገር ግን በማህበረሰቡ ዘንድ መሰራት ያለበትን ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይበልጥ መሰራትና ተማሪዎችም ጥሩ ስነምግባርና ግብረገብነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ሀገር ወዳድ ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ የመምህራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ላይ ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የመምህርነት ሙያ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዴት ይታያል እና መምህራን በሙያቸው ተጠቃሚ ባለመሆናቸውና ኑሮአቸውን ለመደጎም ስራቸውን በመልቀቅ ሙያው አደጋ ላይ በመውደቁ የቀደመ ክብሩን ለመመለስ ምን መደረግ አለበት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዩች ላይ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጓል፡፡

የምክክር መድረኩ አዘጋጅ እንዲሁም ጥናታዊ ፁኁፍ አቅራቢ የሆኑትና  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመምህራን  ትምህርት እና የአመራር ልማት የልህቀት ማዕከል ዲን የሆኑት ዶ/ር አስናቀ ታረቀኝ እንዳሉት የአውደ ጥናቱ ዋና አላማ የመምህርነትን ክብርና ሞገስ እንደገና መመለስና ማኅበረሰቡ ስለመምህራን ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ብሎም መምህራን ማግኘት ያለባቸውን የሙያ ክብር እንዲያገኙ መስራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በሀገሪቱ  ውስጥ መምህራንን ከሚያስለጥኑ ተቋማት ጋር በመሆን በትምህርት ጥራት ላይ የጋራ ስራ እየተሰራ  መሆኑን ጠቁመው ይህ ደግሞ መምህርነት ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በትምህርት ሚኒስቴር የመምህር እና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አሰፋሽ ተካልኝ በሀገራችን ውስጥ ያሉ አምስቱ የልህቀት ማዕከላት ባልተመቻቸና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ እየሰሩ ያለውን ስራ አድንቀው ቀጣይ ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን በማውጣት መሬት  ላይ የወረደ ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን ስራ ለመስራት በመተሳሰርና አንድ በመሆን መምህርነት እንደ ሙያ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚሰጠው ቦታ ከፍ ይል ዘንድ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የግንዛቤ ፈጠራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

በመድረኩ የሁለተኛ ቀን ውሎ የመምህርን የሰው ኃይል አስተዳደር ማዕቀፍን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ያስጠናው ጥናት የጥናቱ ተሳታፊ በሆኑ ምሁራን ቀርቧል፡፡ በጥናቱ አንደተመለከተው መምህራን ለሃገር ዋልታ ለሌሎች ሙያዎች ደግሞ መሰረት በመሆናቸው ከመምህራን ምልመላ ጀምሮ፣ የመምህራን የሙያ ስልጠና ብሎም መምህራንን በስራ ገበታቸው ላይ እንዲቆዩ የማድረግ እና ከጦረታ በኋላ በሚኖራቸው ህይወት አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ከሙያው ሀገሪቷ ማግኘት የሚገባትን ትልቅ ግልጋሎት ማግኘት እንደሚቻል ተነግሯል፡፡ ለዚህም መምህሩን ያቀፈ ስራ እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጡ ምሁራን፣ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የመምህራን ማኅበር አመራሮች፣ በተለያየ ደረጃ የሚያስተምሩ መምህራን፣ በመምህርነት ሙያቸው አርአያነት ያለው ስራን ያበረከቱ መምህራን፣ የወላጅ ማህበር ተወካዮች እና ሌሎች ተገኝተዋል፡፡

 

BDU holds three days workshop on Mitigating Antimicrobial Resistance (AMR) in the water cycle: Analytical methodologies and improving water quality
**********************************************************************
The workshop focused on describing and discussing primary sources of AMR in the water cycle, and the integrated actions needed to mitigating AMR. The workshop aimed to provide a preliminary perspective on the scope of AMR, and to raise awareness about all the factors related to AMR. It also intended to demonstrate different methods of study and to track and mitigate AMR to and from the environment.

A total of 31 participants from three countries and 12 institutions in Ethiopia and abroad took part in the workshop. Professors from three oversea institutions namely New Castle University, UK, Volcani Center for Agricultural Research Organization, Israel and The Hebrew University of Jerusalem, Israel participated as presenters and demonstrators.On day two of the workshop Lectures on perspectives about AMR research in UK and Israel were presented by Prof. David Graham, Dr Eddie Cytryn and Prof. Edouard Jurkevitch, and practical demonstrations were displayed for the benefit of the participants.

As part of the workshop, participants visited College of Agriculture and Environmental Sciences, Zenzelima Campus of Bahir Dar University. There, Dr David Werner from New Caste University demonstrated water sampling protocols, labeling and issues related to water quality. Water Samples were taken from Abay River and the tap water from BDU and filtered so as to take it to New Castle University and Volcani Center for Agricultural Research Organization for further examination on the amount of anions in the waters and more.

In the workshop a series of lectures, field visits, sampling and practical demonstrations were carried out.

የፊልምና ትያትር ካሪኩለም ወርክሾፕ ተካሄደ
=========================
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩሊቲ የፊልምና ትያትር የስርአተ ትምህርት ቀረጻው ተጠናቆ የአስፈላጊነት ግምገማ ተደርጎበታል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙ የዘርፉ ባለሙያዎች ባቀረቡት የመነሻ ሃሳብ መስረት በታዳሚዎች ውይይት ተደርጎበታል።ዘርፉ ለአካባቢው እጅግ አስፈላጊ መሆኑ በውይይቱ በአትኩሮት የተነሳ ነጥብ ነው። በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ሰራትኞችና ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የመጡ ባልሙያዎችም ተሳትፈዋል።
OXFAM-GB የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት የስራ ጊዜውን በማጠናቀቁ በአማራ ክልል የነበረውን ቆይታ በማስመልከት የምክክር መድረክ በባህር ዳር አካሄደ፡፡
-----------------------------------------------------------------------------------
በሙሉጌታ ዘለቀ
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ OXFAM-GB ተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ አዊ ብሄረሰብ ዞን፣ ዳንግላና ጓንጓ ወረዳዎች ውስጥ ̋Empowering women and improving livelihood through honey value chain ̋ በሚል ርዕስ በማር እሴት ሰንሰለት ዙሪያ ጥናቶችን አስጠንቶ ሴት አርሷደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት እና የመንግስት አካላት በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ ምክክር አደረገ፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በአማራ ክልል የOXFAM-GB ፕሮጅክት ሀላፊ የሆኑት አቶ አለሙ አድማሴ ስለ ፕሮጅክቱ አላማ ከምን እንደተነሳና ምን ለማድረግ እንደታሰበ ለታዳሚው በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል፡፡
 
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዩ ሽፈራው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከውጭ ወደ ሀገራችን የሚገቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በቀላሉ በሀገራችን እንዲመረቱ በማድረግ ሂደት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው በማር ምርት ሰንሰለት ለሚሰሩ ተቋማት ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በሰልጣኞች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስልጠና እና የአቅም ግንባታ ላይ ዩኒቨርሲቲው እንደሚሳተፍ ተናግረው የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡
 
OXFAM-GB የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት በዋናነት ሴት አርሷደሮች በማር ምርት ሰንሰለት ላይ ያላቸውን እምቅ አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙበት ከማድረግም በላይ በማር ምርት ሰንሰለቱ እንዲሳተፋ በማድረግ፣ የንብ ማነብ ሂደት ምን እንደሚመስል ስልጠና በመስጠት፣ የማር ማጣራት ሂደትን በማሳየት፣ ሰምን በማጣራትና ወደ ገበያ በመቅረብ ላይ ሲሰራ መቆየቱ በመድረኩ ላይ የተነገረ ሲሆን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን የንብ ማነብ ክህሎትን በማሳደግና የተለያዩ የስልጠና ሞጅሎችን በማዘጋጀት ለሙያው ከፍተኛ አስተዋፆ እንደነበራቸው ተግልጿል፡፡
 
በአሁኑ ሰዓት OXFAM-GB የተሰኘው ተቋም በአማራ ክልል ላይ የነበረውን ቆይታ በማጠናቀቁ ምክንያት እስካሁን የተጓዘባቸውን የስራ ጊዜያት ተከትሎ ጥናቶችን አስጠንቶ በእለቱ ለውይይት ቀርቧል፡፡ ጥናቶቹም ከፕሮጀክቱ ትግበራ በኋላ በንብ ማነብ ሰንሰለቱ ላይ የመጣውን ውጤት ፣ የንብ ማነብ ግብዓቶችን ለማቅረብ የነበሩ መልካም አጋጣሚዎች እና ተግዳሮቶች በሚሉና በንብ ማነብ ዙሪያ የተለያዩ ሴት አርሷደሮች ባጋጠሟቸው ችግሮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ነበሩ፡፡
 
በውይይቱ ላይ እንደዋና የውይይት ሀሳብ ሆኖ በተወያዮች የቀረበው የንብ ማነቢያ ቦታ ነው፡፡ ማነቢያ ቦታዎች የሰብል እርሻ አቅራቢያ በመሆናቸው በሰብሎች ላይ በሚረጭ ኬሚካል ምክንያትና በሌሎች ውስጣዊ እና ውጫዊ በሆኑ በርካታ ምክኒያቶች የማር ምርት የተፈለገውን ምርት ማግኘት እንዳልተቻለ ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑ የሴት አርሷደሮች ቁጥር እስከ ሦስት ሽህ እንደሚደርስ በውይይቱ ላይ ጥናት አቅራቢና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብይ መንክር ተናግረዋል፡፡
 
በመጨረሻም ተወያዮች የመጡበትን ወረዳ በሚመለከት በቀረቡ ጥናቶች ላይ ትክክል የሆነውንና ይቀራል ያሉትን ሀሳብ በቡድን በመሆን ገምግመዋል፡፡

Pages