Latest News

  በስፔን ባርሴሎና ከፍተኛ የስፖርት ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡  

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከACCeDE Spain Barcelona እና ከETHIO-GAVA(Sport Education and Women Development Enterprise) ጋር በመተበባር የተዘጋጀዉና Youth Sport Development and Professional Training በሚል ርዕስ ሲሰጥ የቆየው ዓለምአቀፍ ይዘት ያለዉ ስልጠና ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

የETHIO-GAVA ድርጅት ኃላፊ የሆኑት አቶ ይመር ሃይሌ እንደተናገሩት ግንቦት ወር 2013ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በእግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ እና በዘመናዊ ስፖርት እድገት ዙሪያ ACCeDE ከተባለው የባርሴሎና ድርጅት ጋር ከሐምሌ 12-17/2013ዓ.ም ድረስ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ በተለይም ቅርጫት ኳስ እና እግር ኳስ ከስፔን ካታሎን አንደኛ ደረጃ ፕሮፌሽናል አሰልጣኞችን በማምጣት የአካዳሚ መምህራንን ጨምሮ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመረጣቸው በአማራ ክልል ለሚገኙ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች፤ የፌዴራልና የአማራ ክልል ፌዴሬሽን አመራሮች እና ከባሕር ዳር ከተማ አስተደደር ለመጡ ስፖርተኞች ስልጠናው ተሰጧል፡፡ የስልጠናው ዋና ትኩረት በአለም ላይ የታወቁት ስፔን ባርሴሎና ካታሎናዊያን በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ያረጉበትን የአሰለጣጠን ዘዴ ልምድ ለመቅሰም ነው ብለዋል፡፡ 

ኃላፊው አያይዘውም በታዳጊ ፕሮጀክት ላይ እግር ኳስ፣ ቮሊቮል፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ባድሜንተንና አትሌትክስ ሠልጣኝ ወጣቶች ለስፖርት ማዘውተሪያ የሚውል አልባሳትን ከማበርከት ባሻገር ለስፖርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ማለትም የእግር፣ የቅርጫት፣ የእጅ እና የቫሊቮል ኳሶችንና ለልምምድ የሚያገለግሉ እቃዎችን ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡ እነዚህ ድጋፎች በተደረሰው ስምምነት መሰረት ለ2 ዓመት የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

የስፖርት አካዳሚ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ዲን የሆኑት ዶ/ር ተከተል አብርሃም ለተሳታፊ ሰልጣኞችና የፌዴሬሽን አመራሮች ወደፊት ስፖርቱን በጋራ ለማሳደግና ዘመናዊ ስፖርትን ለማሳደግ በሳይንስና በምርምር የተደገፈ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራትና በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የስፖርት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና ፌዴሬሽኖች ከዚህ ልምድ በመዉሰድ ለሀገራችን ስፖርት እድገት የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲወጡ ም/ዲኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዲን ዶ/ር ዳኛቸዉ ንግሩ በመርሃ-ግብሩ መጠናቀቂያ ላይ ለአሴዴና ኢትዮ-ጋቫ አመራሮችና አሳልጠኞች ላደረጉት ድጋፍና ስልጠና አመስግነዋል፡፡ ከስፔን የመጡት ልዑካን በባሕር ዳር ከተማ ዉስጥ የሚገኘዉን የተስፋ ልማት ማህበር የህጻናትና አረጋዊያን ማዕከል የጎበኙት ልዑካኑ በቀጣይ አብሮ ለመስራት ቃል መግባታቸዉን ዶ/ር ዳኛቸዉ ጠቁመው ስለተደረገዉ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በዩኒቨርሲቲዉና በአካዳሚዉ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በእለቱ ተሳታፊዎች፤ የአሴዴ ልዑክ እና ከፌዴሬሽን የመጡ አመራሮች በስፖርት አካዳሚው በተዘጋጀው ቦታ ላይ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡

በመዝጊያ መርሃ-ግብሩም ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቋል፡፡    

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሀገራችን ላጋጠማት የህልውና ዘመቻው የሚውል ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ተስማሙ

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አሸባሪው እና ክሀዲው የትህነግ  ቡድን በሀገራችን ኢትዮጵያ የደቀነውን  የህልውና አደጋ ለመመከት የወር ደመወዛቸው ከ33ሚሊዮን ብር በላይ  ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታወቁ፡፡ ተሳታፊዎች የሀገር ድንበርን ለማስከበር በጦር ግንባር ለሚዋደቀው ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በገንዘብም ሆነ በሎጀስቲክ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን በጥልቅ ሀገራዊ  ስሜት ውስጥ ሆነው ተናግረዋል፡፡

 

ውይይቱ የተካሄደው በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባሉ በሁሉም ግቢዎች በሚሰሩ ሰራተኞች ሲሆን በተመሳሳይ የማዕከላዊ ሰራተኞች በጥበብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይታቸውን አካሂደዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እና የተማሪዎች ዲን የሆኑት ዶ/ር ምንይችል ግታው ሲሆኑ በክልል ደረጃ  “የአማራ ሕዝብ ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ሰነድ ዶ/ር ምንችል ግታው ለውይይቱ መነሻ ሀሳብ ለተወያዮች አቅርበዋል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች  የቀረበውን ሰነድ መነሻ በማድረግ በወቅታዊ ሀገራችን ለህልውና ዘመቻው ከገንዘብ፣ ከጉልበት ባሻገር የሕይወት መስዋእትነት ለመክፈልም መዘጋጀታቸውን በቁጭትና በሞቀ የሀገራዊ ስሜት ተናግረዋል፡፡

 

ለመላ ኢትዮጵያዊያንና ለክልላችን ካንሰር የሆነውን የትህነግ ቡድን ከስሩ ነቅሎ ለመጣል የሚደረገው የትግል እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ካልተደረገ ጦርነቱ በዘገዬ ቁጠር በሀገራችን ውስጥ የተለየ ፍላጎት ያለቸው የሀገራችን ጠላቶች የምዕራባውያን እጅ መርዘም በኋላ ዋጋ እንዳያስከፍለን ሊታሰብበት እንደሚገባ ተወያዮች ተናግረዋል፡፡  የዩኒቨረሲቲው ማህበረሰብ  በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማየት እንዳይደናገር በመንግስት ሚዲያዎች የሚወጡ ወቅታዊ መረጃዎችን መከታተል እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ እና በተለያየ ምክንያት ከሰራዊቱ የተቀነሱ የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች በህልውና ዘመቻው ለመሳተፍ ተመዝግበው እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ላይ የምናውቀውን ያክል ግልፅነት ለመፍጠርና እንደ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ እና እንደ ዜጋ ምን አይነት ድጋፍ ማድረግ እንችላለን በሚለው ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ወደ ተግባር ለመግባት አይን ከፋች ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከሰራተኛው ለተነሱ ጥያቄዎች ዶ/ር ፍሬው እና  ዶ/ር ምንችል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

 

 

 

Nile Talk Forum 11: Eastern Nile System Under Three Different Water Apportionment Alternatives: Colonial Era, the Washington DC and Equitable Share
Date: August 10, 2021 @ 8AM EST
Speaker: Mr. Yared Bacha Gari | Bahir Dar Institute of Technology (BiT), Bahir Dar University
To Register for Forum 11 Use the link:
ችግኝ ተከላ በምሁራን
በሙሉጎጃም አንዱዓለም
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የአረንጓዴ አሻራን "ሀገር በቀል ችግኞችን በመትከል የህዳሴ ግድባችንን ከደለል እንጠብቃለን" በሚል መሪ ቃል አስሩም በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች በተገኙበት በብር አዳማ ተራራ ላይ ችግኝ በመትከል አክብሯል፡፡
የችግኝ ተከላውን ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ተራራው የውሃ ማማ መሆኑንና ዩኒቨርሲቲው ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ጀምሮ እየሰራበት ያለ ቢሆንም በተለየ መልኩ እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሳይንሳዊ አንድምታውን ጠብቆ በመሰራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፕሬዘዳንቱ አክለውም የሚተከሉት ብዝሃ- እፅዋቶች አገር በቀል መሆናቸውንና ለአካባቢው ተስማሚ እንደሆኑ በጥናት የተረጋገጡ መሆናቸውን አስገንዝበው አስሩም የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም ባሕር ዳር፣ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ታቦር፣ጎንደር፣ ወሎ፣ ደባርቅ፣ ወልድያ፣ እንጅባራና መቅደላ አምባ በተመደበላቸው ስፍራ ላይ ችግኞችን በተገቢው መንገድ መትከል እንዳለባቸው ኃላፊነት ሰጥተዋል፡፡
የቀድሞ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባልደረባና አሁን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአብክመ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው ከተለያዩ አካባቢዎች ጥሪውን አክብረው ለመጡት ምስጋና አቅርበው አረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ ጥሪ ቢሆንም ወቅታዊ እንዳይሆንና በዘላቂነት ሊተገበር የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማስከተልም ዩኒቨርሲቲው በብር አዳማ ተራራ ላይ እያከናወነ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት አመስግነው ከዛሬ በፊት በቋሪት ወረዳ ስር ያለውን ተራራ ያለማ ሲሆን ዛሬ በተመረጠው የይልማና ዴንሳ ወረዳ ስር ያለውን ተራራ ለማልማት በተያዘው እቅድ መሰረት በተግባር መታየቱ ይበል የሚያሰኝ ስራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የሚተከሉት ዕፅዋቶች አገር በቀል ስለሆኑ ስራው በድህረ ምረቃ ተማሪዎች በጥናት የተደገፈ እንዲሆንና ለወደፊት ተራራው ለምቶ የምርምር ጣቢያ እንዲሆን ለዩኒቨርሲቲው አሳስበው የዚህን ዓመት የችግኝ ተከላ ልዩ የሚያደርገው ሃገራዊ ምርጫና የህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተከናወኑበት ማግስት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በየአካባቢያቸው ተጋላጭ ቦታዎችን በማልማት አባይን ከደለል የመከላከል ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዶ/ር ሙሉነሽ በአንክሮ ተናግረዋል፡፡
የይልማና ዴንሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስናቀው ቢሰማኝ ወረዳው 35 ቀበሌ ያለው፣ሶስቱንም የአየር ንብረት (ደጋ፣ወይና ደጋና ቆላ) አካቶ የያዘ፣ምርትና ምርታማነትን ያሳደገ እንዲሁም በሰብል ምርትም ሆነ በእንስሳት እርባታ ከፍተኛ አቅርቦት ያለው መሆኑን ብሎም በትምህርትም ሆነ በጤናው ዘርፍ ጠንካራ ስራ የሚያከናውን ወረዳ እንደሆነ በሰፊው አስተዋውቀዋል፡፡
በማስከተል ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለወረዳው በርካታ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልፀው ከአሁን በፊት ለ19 ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ጀምሮ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ከታላቅ ምስጋና ጋር ተናግረዋል፡፡
ችግኝ ተከላውም በያዝነው የክረምት ወቅት የዛሬውን ሳይጨምር በተለያዩ ጊዜአት በተጋላጭ ቦታዎች ላይ የተተከሉት ችግኞች 73% ማሳካታቸውን ገልፀው ዛሬ የተተከለበት ተራራ በጣም ተጋላጭ ስለሆነ የብር አዳማን ተራራ ማልማት ጎጃምን ማልማት እንደሆነ አስረድተው ባሕ ዳር ዩኒቨርሲቲ ለወደፊት የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስፍራው ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት በጥናት አስደግፈው ምሁራኖች ያቀረቡ ሲሆን ከተለያዩ ቦታዎች ለመጡ እንግዶች የምስክር ወረቀት፣ ዩኒቨርሲቲው እስካሁን በብር አዳማ ላይ ያከናወናቸውን ነገሮች የሚያሳይ ቪዲዮ የያዘ ፍለሽ፣ የአብሮነት መገለጫ የሆነውን የባሕር ዳር አገልግልና ጋቢ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንትና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ ም/ ፕሬዘዳንት በዶ/ር ተስፋዬ ሽፈረው አማካኝነት በስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ታዳሚዎች ከአስሩ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡና ከፌደራል እንዲሁም ከክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተወከሉ እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የበላይ አመራሮች ሲሆኑ ቅኔ በሐይማኖት አባቶች ተዘርፎ ለቀጣዩ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ አዘጋጅ ወሎ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ተለይቶ ተጨማሪ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊቲ (Urology) ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሄደ

*********************************************************************************************

በሙሉጌታ ዘለቀ

የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመጡ ባለሙያዎችና የዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመሰብሰቢያ አዳራሽ የፕሮግራም መክፈቻ መርሃግብር ተካሂዷል፡፡

መርሃ ግብሩን በንግግር ከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ በጤናው ዘርፍ ያሉ ስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን ለመክፈት ከስርዓተ ትምህርት ቀረፃ ጀምሮ መሳሪያዎችን እና ግብአት ለማሟላት ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ችግሮችን ተቋቁሞ ፕሮግራሙን እንዲሳካ ላደረጉ የኮሌጁን የበላይ ኃላፊዎችና ሰራተኞችን አመስግነዋል፡፡

በሀገር ደርጃ የተያዘውን የጤናውን ዘርፍ የማሳደግ እቅድ የሚሳካው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በሚያደርጉት ጥረት በመሆኑ ኮሌጁ ተጠናክሮ ከሀገር ውጭ የሚደረጉ ህክምናዎችን ለማስቀርት እንዲቻል ዩኒቨርሲቲውም ከበጀት ጀምሮ የሚያስፈልጉትን ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ አክለውም ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ አሁን ባለው ሁኔታ ህክምና የሚሰጥባቸው ክፍሎችና በየጊዜው የሚከፈቱ ፕሮግራሞችን እንዲሁም የወደፊቱን ታሳቢ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ለፌደራል እና ለክልል ቢሮዎች የማስፋፊያ ጥያቄ ቀርቦ 138 ሄክታር የማስፋፊያ ቦታ መፈቀዱን በፕሮግራም መክፈቻ መርሃግብር ላይ ተናገረዋል፡፡

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዩሮሎጂስትና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አንዱዓለም ደመቀ እና ዶ/ር መሳይ መኮነን  በፕሮግራም  መክፈቻ መርሃግብር ላይ ተገኝተው አዲስ በሚከፈተው የኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ንግግር አድርገዋል፡፡ በፕሮግራሙ የሚሰለጥኑ ባለሙያዎች ለስልጠና ወደ ጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲመጡ ያለምንም ክፍያ ተቀብለወ ስልጠናውን እንደሚሰጡና ኮሌጁን ለማጠናከር የበኩላቸውን አስተዋፆ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡  

ኮሌጁ ለወደፊት የውጭ አገር ህክምናን በአገር ውስጥ ለማከናውን የሚያስችል አዳዲስ የህክምና ዘርፎችን ለማስጀመር አቅዶ እየሰራ መሆኑንና ለUrology  ስልጠና ማስጀመሪያ የተገዙ የህክምና እቃዎች በጣም  ዘመናዊ በመሆናቸው ሰውነት ሳይከፈት ከብልት ጀምሮ ኩላሊትን ማከም የሚያስችሉ በመሆናቸው ዋጋቸውም የዚያኑ ያክል ውድ በመሆኑ አገልግሎት ሳይሰጡ በአያያዝ ችግር እንዳይበላሹ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጌዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ በፕሮግራሙ መዘጊያ ላይ እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  የሚያደርገውን የስራ እንቅስቃሴ ጥቅሙ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም በመሆኑ ኮሌጁ ከዚህ የበለጠ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ በ2014 ዓ.ም የሚያከብረውን የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ አስመልከቶ ውይይት አካሄደ

*********************************************************************************************

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የኮሌጁ ማህበረሰብ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ሐምሌ 11-12/2013 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ  የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ  ዲን  የሆኑት ዶ/ር ታደሰ መለሰ የቀድሞው የባሕር ዳር መምህራን ኮሌጅ (አካዳሚ ኦፍ ፔዳጎጂ) በ1965 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር በዩኒስኮ እና በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ስምምነት እንደተቋቋመ እና በወቅቱም የመምህራን ትምህረት አካደሚ ይባል እንደነበር አውስተው ይህ አንጋፋ ኮሌጁ ከምስረታው ጀምሮ ያከናወናቸውን ስራዎች እና የኮሌጁን ታሪክ ለተተኪው ትውልድ ሰንዶ ማስቀመጥ ተገቢ መሆnuን ተናግረዋል፡፡

በመጭው ዓመት ኮሌጁ የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን እና ለዚህም የኮሌጁ አንጋፋ መምህራን ውይይቱ ላይ በሰጡት አስተያየት መሰረት የተለያዩ አራት ንዑስ ኮሚቴዎች ተመርጠዋል፡፡ የተመረጡት ኮሚቴዎች ኮሌጁ ከተመሰረተበት ዓመት ጀምሮ ያለውን ታሪክ ማዘጋጀትና መሰነድ፣ የኮሌጁን ታሪክ በዶክመንታሪ መልክ አዘጋጅቶ በዌብሳይት ማስቀመጥ እና በኮሌጃችን የተማሩ በሀገሪቱ ያሉ ታላላቅ ምሁራንን በ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮበልዮ ክብረ በዓል ላይ እንዲገኙ ማድረግ የሚሉ የስራ መርሃ-ግብር እንደተሰጣቸው ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ የልህቀት ማዕከል ሆኖ መመረጡን እንዲሁም  መምህራን የሚሰሯቸው የምርምር ስራዎች በተለያዬ ጊዜ በታዋቂ ጆርናሎች መታተማቸው ፣  የኮሌጁ ተመራማሪ መምህራን የሚሰሯቸውን የምርምር ስራ የሚታተሙበት ጆርናል አክርድቴሽን (እውቅና ያለው ጆርናል ኮሌጁ  እንዲኖረው) ማድረጉ  እንዲሁም ኮሌጁ 38ኛውን ዓመታዊ አለማቀፍ የግንቦት ሴሚናር በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑ በ2013 ዓ.ም ከተሰሩ ስራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ ማህበረሰብ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ውይይት በኮሌጁን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ላይ አንጋፋ መምህራን እና ሁሉም የኮሌጁ ማህበረሰብ ባሉበት ውይይት አድርጎ መስተካከል የሚገባቸው ነጥቦች ተስተካክለው ስትራቴጂክ እቅዱ ከአምስት ዓመት ወደ አስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ  ሆኖ እንዲዘጋጅ በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡

በኮሌጁ የሚያገለግሉ ነባር መምህራን እና  በያዝነው ዓመት ተቀጥረው ኮሌጁን የተቀላቀሉ አዳዲስ መምህራን እንዲሁም በተለያየ እርከን ላይ ሆነው የሚያገለግሉ  የአስተዳደር ሰራተኞችን ለመተዋወቅ እድል የፈጠረ የውይይት መድረክ በመሆኑ በዓመቱ መጨረሻ  ላይ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

 

 

የተማሪዎች ምረቃ
===========
በሙሉጎጃም አንዱዓለም
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሀምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ፕሮፌሰር ተከስተ ዮሐንስ በክብር እንግድነት በተገኙበተት በደመቀ ስነ-ስርዓት አስመረቀ፡፡
በምረቃ ስነ-ስርአቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂዎች ለቤተሰቦቻቸውና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዚያት የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ለሀገሪቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፕሬዘዳንቱ አክለውም በቅርቡ በተካሄደው አገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን መታጨቱ በሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት ተመዝኖ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች የምርምር ውጤታቸው ምን ያህል ችግር ፈች እንደሆነና የማንን ተግዳሮት እንደፈታ እራሳቸውን እንዲጠይቁ፣ እንዲሁም በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ የኪነ- ሕንፃ (Architecture) ተመራቂዎች ውብ የህንጻ ዲዛይን እንደሚሰሩ እንደሚያውቁ የተናገሩት ፕሬዝደንቱ አባቶቻችን የሰሩትን የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን መጠገንን እንዲያስቡትና የሀገሪቱን ጉልህ ችግር እንዲቀርፉ አሳስበው የወደፊት ህይወታቸው የተቃና እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳው የኢትዮጲያ የሳይንስ አካዳሚ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ለተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ተመራቂዎች የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፈው ለዚህ መብቃታቸው ያላቸውን ፅናት እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በማስከተል ዩኒቨርሲቲው በአገር አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎችን የመለየት ስራ በቅርቡ ተካሂዶ የላቀ ውጤት በማስመዝገቡ ግዙፍነቱን ያስመሰከረ እንደሆነ ተናግረው የዕለቱን ምረቃ ልዩ የሚያደርገው አገር አቀፍ የምርጫ ስርዓት ያለምንን ተግዳሮት በተከናወነበት ማግስትና የታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በሚከናወንበት ወቅት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች የትምህርቱን ዓለም ጉዞ ጨርሰው ወደ ስራው ዓለም የሚሽቀዳደሙበት ወቅት ላይ በመሆናቸው ባካበቱት እውቀትና ክህሎት ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ በአደራ መልክ ቁልፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የምረቃውን ስነ ስርዓት ያስፈፀሙት የዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራርና አልሙናይ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ፀጋየ ሲሆኑ ተመራቂዎች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የተማሩ 725 ሴት እና 1638 ወንድ በድምሩ 2363 መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከነዚህ መካከል በተለያየ ምክንያት ምረቃቸው የዘገየ 6 ተመራቂዎችን ጨምሮ 28ቱ የሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በመርሀ-ግብሩ ላይ በምርምር ስራቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የድህረ ምረቃ ተመራቂዎች በክብር እንግዳውና በዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች የእውቅናና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ሁሉም የሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂዎችም መድረክ ላይ በመቅረብ የምረቃ ስነ ስርዓታቸውን አከናውነዋል፡፡ በመጀመሪያ ዲግሪ የኪነ- ሕንፃ (Architecture) የትምህርት ዓይነት ከተመረቁት መካከል እጩ ተመራቂ ገሊላ ተመስገን 3.5 አማካይ ውጤት በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
በምረቃ ስነ-ስርአቱ የአማራ ክልል የፖሊስ ማርሽ ባንድ የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችንና የሰልፍ ትሪኢቶችን ያቀረበ ሲሆን የፖሊስ የሙዚቃ ባንዱም የእንኳን ደስ አላችሁ እና ሌሎች አዝናኝ ሙዚቃዎችን አቅርቧል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ላይ ተሳተፈ
--------------------------------------------------------------------------
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያውን የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ወደ “እውቀት መር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ሀሳብ ሐምሌ 05/2013 ዓ.ም. ያስጀመረ ሲሆን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም በፕሬዚደንቱ፣ ምክትል ፕሬዝደንቶችና ሳይንቲፊክ ዳሬክተሮች እንዲሁም በሌሎች አመራሮችና የኤግዚቢሽን አስጎብኝዎች በመወከል ተሳታፊ ሆኗል፡፡
ኮንቬንሽኑ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ርዕሰ ብሔር ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን በኤግዚብሽን ጉብኝት መርሃ ግብር ላይም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ይዟቸው የቀረበባቸውን የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የፈጠራ ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡ በዕለቱም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራዎች በተለያዩ ሚኒስትሮች፣የግል እና የመንግስት መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ተጎብኝተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለኤግዚቢሽን ካቀረባቸው ስራዎች መካከልም በአግሮ ሜካናዜሽን፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን፣ በጤና፣ በጨርቃጨርቅ እና ፋሽን ዲዛይን እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያከናወናቸው የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የፈጠራ እና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ይገኙበታል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ሌሎችም የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተለያዩ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የፈጠራ ስራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡ ሲሆን የእርስበርስ ትስስር እና የልምድ ልውውጥ እየተካሄደበት ይገኛል፡፡
ኮንቬንሽኑ እስከ ሃምሌ 8/2013ዐ ዓ.ም ድረስ የፈጠራና የምርምር ስራዎችን የማበረታታት፣ እዉቅና የመስጠትና ትስስር የመፍጠር ዓላማውን እያሳካ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

Faculty Staff and Graduate students take Part in a Global North-South virtual Dialogue with counterparts at the University of Klagenfurt, Austria

**********************************************************************

Faculty staff and graduate students’ participated in a north-south dialogue on a theme of global citizenship education with Austrian counters parts at the University of Klagenfurt, Austria. The discussion was held as part of a series of dialogue platforms launched under the growing cooperation between the Faculty of Social Sciences and the University of Klagenfurt, Austria. Held on 6/19/2021, the discussion started with a lecture provided by Dr. Kalewongel Minale titled “Global Citizenship Education – a view from Africa”. Additionally, five graduate students, namely, Mohammed Ahmed, Workeneh Genet, and Lemma Tamene, from the Political Science MA Program, as well as Denekew Bayable and Bisetegne Nega, from the MA program in Peace and Conflict Studies, gave a presentation on a range of topics, including Nationalism as a threat to Global Citizenship in the Global South, The Politics of International Intervention in Northern Ethiopia, “Proliferation of Small Arms and Light Weapons in Ethiopia, Current Issues Affecting Ethiopia, and Media for Global Peace.

More than 42 staff and students from the University of Klagenfurt took part in the event which was held virtually.

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ለዳኞች ስልጠና ሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በባህር ዳር እና ዙሪያዉ ለሚገኙ የሶስት ወረዳ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ከሰኔ 5 ጀምሮ በእንጅባራ ከተማ ስልጠና ሰጠ፡፡

የተሰጠዉ ስልጠና በወንጀለኛ ስነ-ስርዓት ሕግ እና በማስረጃ ሕግ ዙሪያ ሲሆን በስልጠናዉ ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ወረዳ ፍርድ ቤት፣ ከጎንጅ ቆለላ እና ከአዴት ወረዳ የተወጣጡ 35 ሰብሳቢ ዳኞችና ዳኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በስልጠናዉ የሕግ ትምህርት ቤቱ ዲን የእንኳን ደሕና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸዉም ፍርድ ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ዘብ እና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዋስትና ስለሆኑ የሕግ የበላይነት እና የፍትህን ተደራሽ የማረጋገጥ  ሚናቸዉን በተገቢዉ መንገድ መወጣት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል፡፡ የስልጠናዉ ግብ ሙሉ በሙሉ  ሊሳካ የሚችለዉ ዳኞች በስልጠናዉ ያገኙትን እዉቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ለመተግበር ጥረት ማድረግ ሲጀምሩ ስለሆነ በስልጠናዉ የምታገኙት እዉቀት፣ ክህሎትና ልምድ በተግባር መተርጎም ይኖርባቸኋል በማለት አሳስበዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳርና አካባበዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዜዳንት አቶ ኃይለየሱስ የሕግ ትምህርት ቤቶች በአካባቢዉ ከሚገኙ የፍትህ አካላት እጅና ጓንት ሆነዉ መስራት የሚገባቸዉ መሆኑን ጠቅሰዉ በምርምር፣ በአቅም ግንባታ ስልጠና፣ እና አጋርነቶችን በመፍጠር በፍትህ ስርዓቱ ላይ መጫወት የሚገባቸዉን ሚና በተገቢዉ መንገድ መወጣትና በቀጣይም ይህንን እና መሰል ተግባራትን አጠናክረዉ መቀጠል እንደሚኖርባቸዉ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡ ስልጠናዉን የሰጡት የህግ ትምህርት ቤቱ አንጋፋ መምህር ረ/ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ ሲሆኑ ስልጠናዉ በሕጉ አተገባበር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እና ሕጉ በምን አግባብ መተርጎም አለብት የሚለዉን  ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር አስተሳስረዉ ለፍርድ ቤቶቹ የወደፊት ስራ በሚጠቅም መንገድ አቅርበውታል፡፡

ስልጠናዉን የተካፈሉት ዳኞች እና ሰብሳቢ ዳኞች በስልጠናዉ ለወደፊቱ ስራቸዉ የሚጠቅም አስተማሪ ግብአትና ጠቃሚ ትምህርት ማግኘታቸዉን ጠቅሰዉ አሰልጣኙንና የሕግ ትምህርት ቤቱን አመስግነዋል፡፡ አስተያየት ሰጭዎች አክለውም የሕግ ትምህርት ቤቱ ለወደፊቱ የተለያዩ የአቅም ግንባታ እንዲሰራና ጅምሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡ 

Pages