Latest News

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ2012 ዓ.ም የተሰሩ ማህበረሰብ ተኮር የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አስመረቀ፡፡ ለዝርዝሩ ቀጣዩን ሊንክ ይከተሉ፡- https://www.facebook.com/bitpoly/posts/1115642688836900

የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ ርክክብ ተካሄደ
********************************************
በሙሉጐጃም አንዱዓለም
ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ለባህር ዳር ከተማ ትምህርትና ጤና መምሪያ “Frances G. Cosco Foundation (FGCF)” /ኤፍ. ጂ. ሲ. ኤፍ./ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ በጐ አድራጐት ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ርክክብ ተካሄደ።

የመርሐ-ግብሩን መጀመር ይፋ ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕ/ር የሺጌታ ገላው ለታዳሚዎች የእንኴን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡አክለውም ወቅቱ ሀገራችንን ጨምሮ ሁሉም የዓለም ህዝብ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ፍልሚያ የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመው ለተደረገው ድጋፍ በኮሌጁ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ድርጅቱ ከአሁን በፊት ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ለሌሎች ተቋማት በርካታ ድጋፍ እንዳደረገና ድጋፉ ወረርሽኙ ከሚጠበቀው በላይ በጨመረበት ወቅት መሆኑ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ አውስተው በሆስፒታሉ ስም ቢሰጥም ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ አገልግሎት እንዳለው በመግለፅ ለወደፊት ቀጣይነት እንዲኖረው አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋና አቅርበው ድርጅቱ ከአሁን በፊት “ትምህርት ለለውጥ” በሚል መሪ ቃል ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር አራት ትምህርት ቤቶችን ከተለመደው ወጣ ባለ እና በተሻለ መንገድ እንዲገነባ በማድረግ በርካቶ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በተጨማሪም ሆስፒታሉ መማር ማስተማርን ምርምርን እና የማህበረሰብ አገልግሎትን ሶስቱንም የዩኒቨርስቲውን አምዶች አሳልጦ እየሰራ መሆኑን ም/ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የበጐ አድራጐት ድርጅቱ የአማራ ክልል አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብዮት አሸናፊ ድርጅቱ በአማራ ክልል በተመረጡ 5 ዞኖች እንደሚሰራና ለወደፊትም ተደራሽነቱን እንደሚያስፋፋ ገልፀው ከዩኒቨርሲቲው ጋርም በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል።

አስተባባሪው በማከልም የቀረቡት ቁሳቁሶች 11 አይነት እንደሆኑና ለዩኒቨርሲቲው፣ ለባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ እና ጤና መምሪያ ጭምር በገንዘብ ቢተመን ከ6 መቶ ሺህ ብር በላይ ድጋፍ እንዳደረጉ ተናግረው በክልሉ ለሚገኙ ለ14 ትምህርት ቤቶችም 4 ሰዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስታጥብ ከንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ከቁሳቁሶች መካከል ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ባለሙያዎች አልባሳትና ከንክኪ ነፃ የሆነ የሙቀት መለኪያ እንደሚገኙበት አስገንዝበው ለወደፊት ት/ት ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ት/ቤቶች ቢከፈቱ ተማሪዎችን በምን ዓይነት መልኩ ከወረርሽኙ መታደግ እንደሚገባ እንዲሁም የዓይን ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ለማገዝ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ አስተባባሪው ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሻገር አዳሙ ድርጅቱ በተለይ ትምህርት ላይ መሬት የነካ ስራ በስፋት እየሰራ መሆኑንና 5 ትምህርት ቤቶችን በፍጥነትና በጥራት አስገንብቶ ምቹ ክፍሎችን በመፍጠር አኩሪ ተግባር እንዳከናወነ ተናግረው አሁን ለተደረገው ድጋፍም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ ተስፋ ሞላ በአሁኑ ወቅት በሃገራችንም ሆነ በከተማችን ወረርሽኙ እየተስፋፋ ባለበትና የመከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት በተከሰተበት ወቅት እርዳታው መድረሱ አስፈላጊ ጊዜ ላይ እንደሆነ አስገንዝበው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ርክክቡ የተካሄደው በድርጅቱ አስተባባሪ አቶ አብዮት እና በዶ/ር ተስፋዬ አማካኝነት ሲሆን የጥበበ ጊዮንን ፕ/ር የሺጌታ፣ የባህር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያን አቶ ተሻገር እና የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያን አቶ ተስፋ ተረክበዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አምስት የትምህርት ተቋማት የችግኝ ተከላ አካሄዱ

በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪነት በሶሻል ሳይንስ እና ሂውማኒቲስ ፋኩልቲዎች እንዲሁም ፣ በትምህርትና ስነ ባህሪ ፣ ሳይንስ እና በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጆች  የሚገኙ መምህራንና ሰራተኞች በቤዛዊት ተራራ የችግኝ ተከላ አካሄዱ፡፡

በመርሃ ግብሩ የሶሳይቲ ፎር ኢኮ ቱሪዝም እና ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ሲቪል ማህበር ስራ አስኪሂያጅ ትዝታ የኔአለም እንዳሉት እየለማ ያለው እና በእለቱ ችግኝ የተተከለበት ቦታ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በ225 ሄክታር  መሬት የላንታና  ካማራ አረምን ማስወገድ እና መልሶ ማልማት የ5 ዓመት ፕሮጀክት እየተካሄደበት የሚገኝበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ችግኞቹ አገር በቀል የሆኑ እና ሌሎችም የተካተቱበት ሲሆን በየእለቱ ችግኞችን የሚንከባከቡ ጊዚያዊ ሰራተኞች እንዳሉ ገልፀዋል ፡፡ 

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀገራችን የያዘችውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የመትከል ሰፊ እቅድ ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎችና ቀናት በ2012 ዓ.ም. ከፍተኛ አመራሮችንና መላውን የዩኒቨርሲቲውን እና በአማራ ክልል የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችንም ያሳተፈ ችግኝ የመትከል  መርሃ ግብር እንዳካሄደ ይታወቃል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በባሕር ዳር ቤዛዊት ተራራ ላይ ችግኝ ተከላ አካሄዱ
======================================================
በሙሉጌታዘለቀ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ "የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለል፣ የአባይን ወንዝ እና የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ እንታደግ” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የባህር ዳር ከተማ ም/ከንቲባን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በቤዛዊት ተራራ የችግኝ ተከላ ተካሄደ፡፡

በመርሀ ግብሩ የባሕር ዳር ከተማ ም/ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለከተማዋ እስትንፋሷ መሆኑን አውስተው፣ የጣናንና አባይን ህልውና ለማስቀጠልና ከደለል ለመታደግ ተቋማት በያሉበት ችግኞችን በመትከል የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በተካታታይ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ ዶ/ር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው ችግኞች ፀድቀው ለተፈጥሮ ሐብት ጥበቃና ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያለሙዋቸው ቦታዎች ህብረተሰቡን በባለቤትነት ያሳተፈ መሆን እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ሲናገሩም በጉና ተራራ የተጀመረው የዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢ ጥበቃ ስራ በጮቄ ተራራ ቀጥሎ ባህር ዳር በቤዛዊት ተራራ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ጉዞውን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ችግኞች መፅደቃቸውን መከታተልና የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲሆኑ ማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚጠበቅ ጠቁመው የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ አንፃር ተከታታይ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

አክለውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የላንታና ካማራ /የረኛ ቆሎ/ አረምን ከማስወገድ ጀምሮ በርካታ የልማት ስራዎችን ከሶሳይቲ ፎር ኢኮቱሪዝም እና ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በቀጣይም በተራራው የኬብል ካር ቴክኖሎጂን በመዘርጋት ለተማሪዎች አገልግሎት የማዋል እቅድ እንዳለው ጠቅሰው በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የአማራ ክልል አመራሮች ባሉበት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአባይ ወንዝ ላይ ያወጣውን የአቋም መግለጫ አቅርበዋል፡፡

አመራሮች ከችግኝ ተከላው በፊት ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል /STEM Center/ አጫጭር ስልጠና የሚሰጥበትን ተቋም እና የደንገል ልማት ፕሮጀክት ስራዎችን መጎብኘታቸው ታውቋል ፡፡

 

 “የተባበረ ክንድ ጣናን ለመታደግ”

ሰኔ 19/2012 ዓ.ም

በሙሉጌታ ዘለቀ

------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

"ጣናን ለመታደግ የጋራ፣ የትብብርና የፍቅር አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ወደ ጉና" በሚል መሪ መልዕክት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የደብረታቦር፣ የደባርቅ፣ የጎንደር፣ የእንጅባራ እና የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች የጉና-ጣና ተፋሰስ ቦታዎች ላይ ችግኝ ተክለዋል፡፡

 

የችግኝ ተከላውን ሲያከውኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከጉና ተራራ የሚነሱ ወንዞችና መጋቢ ጅረቶች ተከዜንና ጣናን የሚሞሉ መሆናቸው እና ጉና ተራራን በደን መሸፈን የተፈጥሮ ሃብቶችን ለመጠበቅ ዋስትና መሆኑን መነሻ ያደረጉ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በእለቱም የጉና ተራራ ጣና ተፋሰስ አካባቢን ለማልማት የተደረገ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓትም ተካሂዷል፡፡

 

በዚህ ታሪካዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ አባይና ጣናን ለማዳን በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዳለ ጠቅሰው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም በከፍተኛ የተፋሰስ ቦታዎች ላይ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንና የጉና ተራራ አካባቢ ተኮር የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ምርምሮች እየተሰሩ መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

 

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ፣ ከመጤ አረሞች እንዲሁም ከደለል ለመታደግ ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል ከመሆን ይልቅ በጋራ ሁነው የምርምር ስራዎችን መስራታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የጉና አካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን መስራት ብሎም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አካባቢውን የጋራ የምርምር ማዕከል ማድረግ ጊዜው የሚፈልገው መሆኑን ተናግረው የዕለቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የእንቅስቃሴው መነሻ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

 

 

በተጨማሪም በክምር ድንጋይ ከተማ በሚገኘውና በመከላከያ በተገነባው የደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ ምዕራብ እዝ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግኝ ተከላ ተከናውኗል፡፡ 

 

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የተጀመረው የስድስቱ ዩኒቨርስቲዎች የጉና ተራራ አከባቢን የማልማት የችግኝ ተከላ መረሀ ግብር የመጨረሻ መዳረሻውን ጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር በማድረግ ጉብኝት አካሂዷል፡፡

በዚህ ታሪካዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የስድስቱም ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የዞን አስተዳዳሪዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

 

የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዓመታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ
**************************************************************
የዘንዘልማ ግቢ የአስተዳደር ዘርፍ፡- የጠቅላላ አገልግሎት ፣ የተማሪ አገልግሎት፣ የሰው ሃብት አስተዳደር ፣ የግዥና ፋይናንስ አገልግሎት፣ የንብረት አስተዳደር፣ የፀጥታና ደህንነት ክፍሎች ስራቸውን በማቅረብ ዓመታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄዱ፡፡
በመርሃ ግብሩ የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ታደሰ መኳንንት የዕለቱን ዝርዝር ፕሮግራም ያቀረቡ ሲሆን ግምገማው ለቀጣይ በጀት ዓመት የተሻለ ለመንቀሳቀስ እንደመነሻ የሚሆኑ ሀሳቦችን ለማግኘት እና የነገ እቅድን በተሻለ ለመፈፀም ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ኤክስኪዩቲቨ ዳይሬክተር አቶ ገደፋው ሽፈራው በበኩላቸው ሁሉም የስራ ክፍሎች በያዙት ዕቅድ መሰረት ምን ያህል ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን መገምገማቸው ለቀጣይ በጀት ዓመት ጠቃሚ ግብዓቶችን ከማግኘት ባሻገር በሌሎች ግቢዎች ባልተለመደ መልኩ መቅረቡ ይበል የሚያስብል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዋናነት ከተሳታፊዎች ለተነሱ የግቢው የውሃ እና የመብራት ችግርም ዩኒቨርሲቲው ሰባት አሚት ላይ በከፍተኛ ወጭ 5 ጉድጓዶች አስቆፍሮ በሶስቱ ጉድጓድ ላይ ውጤት እያመጣ ስለሆነ በቅርቡ ይፈታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አሳምነው ጣሰው በተገኙበት የተሻለ ስራ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የኮሌጁ ሰራተኞች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከሶካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በአንድነት በጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ተቋም ድጋፍ የተዘጋጀውን ፐሮጀክት አሸንፈዋል።
****************************************************************************

የፕሮጀክቱ ርዕስ “Eco-engineering for Agricultural Revitalization Towards improvement of Human nutrition (EARTH): Water hyacinth to energy and agricultural crops” የሚል ሲሆን ፕሮጀክቱ ከእንቦጭ ስጋት መጨመር ጋር የተገኘ መሆኑ ወቅቱን የጠበቀ ያደርገዋል፡፡ በሶስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ቅንጂት የሚሰራው ይህ ፕሮጀክት በተዘጋጀው አንድ የጥናት ጭብጥ ዙሪያ ለውድድር ከተላኩ ሰላሳ ትልመ ጥናቶች አሸናፊ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ይህ አለም አቀፍ ምርምር በሶካ ዩኒቨርሲቲ (Soka University) መሪነት የሚካሄድ ሲሆን ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር በሚገባበት ጊዜ የተመራማሪዎችን አቅም ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዉ በእንቦጭ አረም ላይ እያካሄደ ያለዉን ፈርጀ ብዙ ምርምር ወደላቀ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገዉ ይታመናል። ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ ለመግባት የሁለቱን ሃገራት ስምምነት የሚያሰፈልግ ይሆናል።

BDU and Injibara University together with Soka University of Japan win SATREPS project.
**********************************************************************************
Two local Universities, Bahir Dar University and Injibara University, and Soka University from the funder country, Japan, jointly won a timely project titled “Eco-engineering for Agricultural Revitalization Towards improvement of Human nutrition (EARTH): Water hyacinth to energy and agricultural crops”.
Bahir Dar University would like to congratulate and appreciate the experts both from inside and outside who worked relentlessly to win this project. The university believes because of the project there will be knowledge and technology transfer which will help the host country benefit in many ways both from the research process and the research outputs in tacking the problems identified and more.

SATREPS (Science and Technology Research Partnership for Sustainable Development) is a science and technology diplomacy initiative that promotes international joint research between Japan and developing countries using advanced Japanese science and technology. The SATREPS program is a collaboration between JICA, the Japan Science and Technology Agency (JST) and the Japan Agency for Medical Research and Development (AMED).
SATREPS aims to acquire new knowledge that can be utilized for the benefit of society, including for the capacity-building of researchers and research institutes in developing countries based on local needs.

Before the implementation of the project an international agreement needs to be signed between MOFA and the Government of Ethiopia regarding implementation of the project, followed by an agreement on the details of technical cooperation between JICA and the research counterpart(s) in the developing country.
Together, we can change the future!

የኢትዪዺዽያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የባህርዳር ቅርንጫፍ እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዋሸራ ጅኦስፔስና ራዳር ሳይንስ የምርምር ላቦራቶሪ በጭስ አባይ የፀኃይ ግርዶሽ ምልከታ አካሄዱ
--------------------------------------------------------------------------------------------
በቦታው ስለነበረው ሁኔታ እና ስለፀሀይ ግርዶሽ ጠቅለል ያለ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የዋሸራ ጅኦስፔስና ራዳር ሳይንስ የምርምር ላቦራቶሪ ዳይሬክተር ዶ/ር መልሰው ንጉሴ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡
በቦታው ከ12፡20 ጀምሮ በመገኘት እስከ 3፡00 ድረስ ክስተቱን የጨረር መነጸር(solar glass) በመታገዝ ይከታተሉ እንደነበርና የኢትዪዽያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከቦታው በቀጥታ ስርጭት ይልክ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
 
ክስተቱ በአብዛኛው ኢትዮዽያ በተለይም በሰሜን እና ምዕራብ ኢትዮዽያ የተከሰተ መሆኑን አስታውሰው የግርዶሹ አይነት ከፊል(Partial solar eclipse) እና ቀለበታማ( annular solar eclipse) የፀኃይ_ግርዶሽ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡
ስለክስተቱ ምንነት እና አፈጣጠር ሲያብራሩ መሬት በፀሀይ ዙሪያ ስትዞር እና ጨረቃ በመሬት ዙሪያ ስትዞር መሬት፣ ፀሀይ እና ጨረቃ ትይዩ(In a straight line) በሚሆኑበት አጋጣሚ፤ ጨረቃ በመሬት እና በፀሀይ መካከል በመሆን ከፀሀይ የሚመጣውን ጨረር ስታግደው የጨረቃ ጥላ መሬት ላይ ያርፈና የፀኃይ ግርዶሽ ይፈጠራል ብለዋል፡፡
 
የአሁኑ ግርዶሽ ጨረቃ ከመሬት በጣም እርቃ በምትገኝበት ወቅት የተከሰተ ስለሆነ ጨረቃ ሙሉ በሙሉ ፀሀይን ማገድ ስለማትችል ነው ቀለበታማ ግርዶሽ የተፈጠረው ይላሉ፡፡ ሙሉ ግርዶሽ የሚፈጠረው ጨረቃ ለመሬት በጣም ቅርብ በምትሆንበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡
 
በአለም በየዓመቱ ከ2 እስከ 5 የሚደርስ የፀሀይ ግርዶሽ እንደሚከሰት ጠቁመው
ግርዶሹን ለመመልከት የሚያስችል ከመቶ(100) በላይ የጨረር መነጸር (solar glass) ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መሰጠቱን ዳይሬክተሩ አክለው ተናግረዋል፡፡
 
 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከል በይፋ ተከፈተ፡፡

(በሙሉጉጃም አንዱዓለም)

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሳንባ ቆልፍ (ኮሮና ቫይረስ) ለመመርመር የሚያስችል ማዕከል ተከፈተ፡፡

በመክፈቻ መርሐ-ግብሩም ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው ጥሪውን አክብረው ለመጡ እንግዶች ምስጋናና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው የመመርመሪያ ማዕከሉ በአማራ ክልል 6ኛው በባህር ዳር ከተማ ደግሞ 2ኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አክለውም በክልሉ ያሉት አምስት መመርመሪያዎች ከህዝቡ ቁጥር አንፃር ሲታዩ አነስተኛ እንደሆኑና የማዕከሉ መከፈት ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ማሽኑ አውቶማቲክ ሳይሆን በማኑዋል የሚሰራና በአንድ ግዜ 96 ናሙናዎችን የሚቀበል እንደሆነ እንዲሁም ከሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ጀምሮ ለ24 ናሙናዎች (ሁሉም ውጤታቸው ከቫይረሱ ነጻ የሆነ) ምርመራ እንዳካሄደ አስገንዝበው ወደፊት ማሽኑን ወደ አውቶማቲክ ከፍ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ዩኒቨርሲቲው ወረርሽኙን ለመከላከል በርካታ አኩሪ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ገልፀው የዚህ ማዕከል መከፈትም አንዱ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዘዳንቱ አክለውም ኮሌጁ ወረርሽኙን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራ ላለው ስራና ለጤና ባለሙያዎች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ፕሬዘዳንቱ በማስከተል በቴክኖሎጂ ዘርፉም ዩኒቨርሲቲው ያፈራቸው ምሁራን በርካታ ቁጥር ያላቸው የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን አምርተው በማቅረብ ግንባር ቀደም መሆናቸው ዩኒቨርሲቲውን እንደሚያኮራ ጠቅሰዋል፡፡

የመርሃ-ግብሩ የክብር እንግዳና የአ/ብ/ክ/መ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የክልሉ ኮሮናን የመከላከልና መቆጣጠር ግብረ-ኃይል ሰብሳቢ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በርካታ ስራዎችን እንዳከናወኑ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉነሽ እንደገለጹት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ እየሰራቸው ካሉ ተግባራት ጎን ለጎን በእንቦጭም ሆነ በሌሎች ተግዳሮቶች ዙሪያ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ስለሆነ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው የማዕከሉ መከፈት እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነና ለወደፊትም ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሌች ተቋማት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ወረርሽኑን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ማዕከሉ በይፋ ተከፍቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን አብስረዋል፡፡

የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ ሙላቱ መለሰ በበኩላቸው ወረርሽኙ ሀገራችንን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የፈተነ በመሆኑና በዚህ ወቅት ደግሞ በቅንጅት በመስራት ወረርሽኙን ከመዋጋት አንፃር ዩኒቨርሲቲዎች የአንበሳውን ድርሻ ወስደው በመረባረብ በርካታ የሚያስመሰግን ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በርካታ ምሁራንን የያዘ በመሆኑ መጠነ-ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ግንባር ቀደም ተደራሽ ስለሆነና ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ማዕከሉ እንዲከፈት ስላደረገ በጤና ቢሮው ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አቶ ሙላቱ በማስከተል ለወደፊቱ ማሽኑን ወደ አውቶማቶክ የመቀየርና ተቀናጅቶ የመስራት አቅምን ከፍ የማድረጉ ጉዳይ ሊሰመርበት የሚገባ ስለሆነ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ርብርቡን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ በመረሐ-ግብሩ ላይ የመመርመሪያ ላቦራቶሪው ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን ናሙና የሚወስዱ 20 የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዳሉና እነሱ ጎን ለጎን ሌሎችንም እያሰለጠኑ እንደሚገኙ መረዳት ተችሏል፡፡

Pages