የ2013 ዓ.ም የባድሜንተን ስፖርት ውድድር እየተካሄደ ነው
የ2013 ዓ.ም የባድሜንተን ስፖርት የኢትዮጽያ ሻምፒዮና ውድድር ከሚያዚያ 2/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዘንዘልማ ግቢ እየተካሄደ ሲሆን በውድድሩ 5 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ። በመርሃ ግብሩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ከኦሮምያ ክልል፣ ከአማራ ክልል፣ ከሲዳማ ክልል፣ ሶማሌ እና ሃረሪ ክልል የመጡ ስፖርተኞች ተሳታፊች ናቸው።
ባድምንተን አካታች ስፖርት እንደመሆኑ እድሜን እና ጾታን ሳይገድብ ሁሉንም ማሳተፍ የሚችል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ወ/ሮ እታለማሁ ተሰማ እንዳሉት በዘንድሮው ውድድር ከ 2 ከተማ አስተዳድሮች እና 5 ክልሎች በተጨማሪ በፓራ ባድምነተን በድንክየ ወይም ድዋርፍ እና በዊልቸር ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል፡፡ ይህ ሲሆን የተሳትፎ እድል ከመስጠት አንጻር እና ውድድሩን እንደማስታወቂያ ለመጠቀም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል ።
የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ ውድድሩ እንደማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ወጣቶችን አንድ ላይ የሚያገናኝ በመሆኑ ብሄር ብሄረሰቦች በጠባብ አዳራሽ ተገናኝተው ወጋቸውን ባህላቸውን እንዲሁም ታሪካቸውን የሚለዋወጡበት በመሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡ ወጣቶችም ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅመው አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ስለአንዲት ኢትዮጽያ እና ስለአንድነትዋ እንዲያስቡ አሳስበዋል፡፡ አቶ ባዘዘው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን በእጅጉ አመስግነው ወደፊትም ሌሎች ተመሳሳይ ስራዎችን አጠናክሮ እንዲሰራ በማሳሰብ ከተማ አስተዳድሩ ከጎኑ ሆኖ እንደሚደግፈው ቃል ገብተዋል።
አቶ ሰይፉ አሊ ከኢትዮጽያ ባድሜንተን ስፖርት በበኩላቸው ውድድሩ በሰላም የተጀመረውን ያክል በሰላም እንዲጠናቀቅ መልካም እድል ተመኝተው በዚህ ውድድር ጠንካራ እና ጥሩ ልጆችን ለማየት እና በአፍሪካ ደረጃ ለሚያካሂዱት ውድድሮች የሚበቁ ልጆችን ለመመልመል ለፌዴሬሽኑ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ውድድሩም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ጋር አብሮ ለመስራት የተደረሰው የጋራ ስምምነት አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ ሰይፉ አክለውም ስፖርት ሁሌም መርሁ ወንድማማችነት እና ሰላም እንዲሁም ወዳጅነት በመሆኑ ሁሉም ስፖርተኞች ከተለያዩ ክልሎች ቢመጡም በኢትዮጽያዊነት ስሜት ውጤታማና በሀራዊ እንድምታው ጉልህ የሆነ ትግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ወ/ሮ እታለማሁ ተሰማ የኢትዮጽያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽንን፣.የክልሉን ባድሜንተን ፌዴሬሽንና.የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚን መርሃ ግብሩን በማስተባበሩ፤ የዩኒቨርሲቲው ግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅን ደግሞ ለልኡካን የመኝታ እና ጠቅላላ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጉ በአጠቃላይ ወድድሩ የተሳካ እንዲሆን ላደረጉት በሙሉ ፌዴሬሽኑን በመወከል ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
ውድድሩ እስከ ሚያዚያ 10/ 2013 ድረስ የሚቀጥል እንደሆነ ታውቋል።