Urologyሰብ ስፔሻሊቲ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊቲ (Urology) ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሄደ

*********************************************************************************************

በሙሉጌታ ዘለቀ

የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመጡ ባለሙያዎችና የዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመሰብሰቢያ አዳራሽ የፕሮግራም መክፈቻ መርሃግብር ተካሂዷል፡፡

መርሃ ግብሩን በንግግር ከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ በጤናው ዘርፍ ያሉ ስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን ለመክፈት ከስርዓተ ትምህርት ቀረፃ ጀምሮ መሳሪያዎችን እና ግብአት ለማሟላት ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ችግሮችን ተቋቁሞ ፕሮግራሙን እንዲሳካ ላደረጉ የኮሌጁን የበላይ ኃላፊዎችና ሰራተኞችን አመስግነዋል፡፡

በሀገር ደርጃ የተያዘውን የጤናውን ዘርፍ የማሳደግ እቅድ የሚሳካው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በሚያደርጉት ጥረት በመሆኑ ኮሌጁ ተጠናክሮ ከሀገር ውጭ የሚደረጉ ህክምናዎችን ለማስቀርት እንዲቻል ዩኒቨርሲቲውም ከበጀት ጀምሮ የሚያስፈልጉትን ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ አክለውም ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ አሁን ባለው ሁኔታ ህክምና የሚሰጥባቸው ክፍሎችና በየጊዜው የሚከፈቱ ፕሮግራሞችን እንዲሁም የወደፊቱን ታሳቢ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ለፌደራል እና ለክልል ቢሮዎች የማስፋፊያ ጥያቄ ቀርቦ 138 ሄክታር የማስፋፊያ ቦታ መፈቀዱን በፕሮግራም መክፈቻ መርሃግብር ላይ ተናገረዋል፡፡

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዩሮሎጂስትና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አንዱዓለም ደመቀ እና ዶ/ር መሳይ መኮነን  በፕሮግራም  መክፈቻ መርሃግብር ላይ ተገኝተው አዲስ በሚከፈተው የኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ንግግር አድርገዋል፡፡ በፕሮግራሙ የሚሰለጥኑ ባለሙያዎች ለስልጠና ወደ ጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲመጡ ያለምንም ክፍያ ተቀብለወ ስልጠናውን እንደሚሰጡና ኮሌጁን ለማጠናከር የበኩላቸውን አስተዋፆ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡  

ኮሌጁ ለወደፊት የውጭ አገር ህክምናን በአገር ውስጥ ለማከናውን የሚያስችል አዳዲስ የህክምና ዘርፎችን ለማስጀመር አቅዶ እየሰራ መሆኑንና ለUrology  ስልጠና ማስጀመሪያ የተገዙ የህክምና እቃዎች በጣም  ዘመናዊ በመሆናቸው ሰውነት ሳይከፈት ከብልት ጀምሮ ኩላሊትን ማከም የሚያስችሉ በመሆናቸው ዋጋቸውም የዚያኑ ያክል ውድ በመሆኑ አገልግሎት ሳይሰጡ በአያያዝ ችግር እንዳይበላሹ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጌዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ በፕሮግራሙ መዘጊያ ላይ እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  የሚያደርገውን የስራ እንቅስቃሴ ጥቅሙ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም በመሆኑ ኮሌጁ ከዚህ የበለጠ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡