81ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አርበኞች ቀን

81ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአርበኞች ቀን በዓል ተከበረ

[ሚያዚያ 27/2014ዓ/ም፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ]

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዐባይ የቋንቋና ባህል ጥናት ተቋም ከታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል እንዲሁም የውስጥ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከባህል ማዕከል ጋር በመተባበር 81ኛውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አርበኞች ቀን በዓል የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በጥበበ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከበረ፡፡ 

በዓሉን በተመለከተ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት ብሔራዊ በዓሎቻችን ስንዘክር የትናንት ማንነታችን፤ ለዛሬ የደረስንበት  እና ለነገ ደግሞ መድረስ የሚጠበቅብንን መነሻ አድርገን ልንማማርባቸው የሚገባ ስለሆነ ዩኒቨርስቲዎችም የአካዳሚክ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ምን እንማራለን፣ ዩኒቨርስቲዎችስ ታሪክን ከመሰነድ እና ለቀጣይ ትውልድ ከማስተላለፍ አንፃር ምን ድርሻ አለባቸው የሚለውን ምሁራዊ ውይይት በማድረግ አስተዋጽዖ ለማበርከት ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም በታሪክ እንደሚታወሰው በዛሬዋ ቀን ጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች የድል ችቦዎቻቸውን ያበሩበት ቀን ሲሆን የጣሊያንን ሰንደቅ ዓላማ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በብሔራዊ ቤተመንግስት የሰቀሉበት ቀን በመሆኑ ሁላችንም ጀግኖች አርበኞቻችን የምናወድስበት፣ የምናመሰግንበት እና ከነሱ ልምድ ተምረን እያንዳንዳችን በየመክሊታችን አስተዋፆ የምናደርግበት ነው ብለዋል፡፡   

በስነ-ስርዓቱ ሁለተኛው የኢትዮ-ጣልያን ጦርነት በአዶልፍ ፓርላሳክ እይታ በሚል ርእሰ ጉዳይ በዶ/ር ዋጋው ቦጋለ ከታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል እንዲሁም አርበኛ ደራሲያንና ተጋድሏቸው በሚል ርእስ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴን በማሳያነት በመግለፅ ዶ/ር ሞገስ ሚካዔል ከአባይ የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን በፅሁፍ አቅራቢዎች እና መድረኩን በመሩት በዶ/ር ፈንታሁን ከታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም ከአቶ አሰፋ አሊ ‹‹አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ- መፅሐፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት ሐዲስ (1962)›› እንዲሁም ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ- የዓለም ጅኦግራፊ (1920)›› የሚሉ መፅሀፍትን ለዓባይ የቋንቋና የባህል ጥናት ተቋም ተበርክቷል፡፡