3ኛው የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምክክር መድረክ

3ኛው የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተካሄደ
 
(ሀምሌ 24 /2014ዓ.ም፣ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-BDU) የፌደራል ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና ከባለደርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ አዳራሽ ውይይት ተካሄደ፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ዩኒቨርሲቲው እየሰራቸው ያሉትን ዋና ዋና ተግባራት ለተወያዮቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ግቢዎችን ውብና ማራኪ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን፣ ለባሕር ዳር ከተማ እና ለአካባቢው ማህበረሰብ ችግር ፈቺ የሆነ ጥናትና ምርምር እያደረገ እንደሆነ፣ ዩኒቨርሲቲው ግንባር ቀደም የምርምር ዩኒቨርሲቲ እና የልህቀት ማዕከል ለመሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም እያንዳንዱ ግቢ በውስጡ የሚያከናውናቸውን አንኳር አንኳር ስራዎች አብራርተዋል፡፡
 
የመንግስት ግዥ እና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በበኩላቸው በዚህ የምክክር መድረክ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችንና ም/ፕሬዚዳንቶችን መሰብሰብ ያስፈለገበት ምክንያት ግዥ የኃላፊዎች ሥራ በመሆኑና ያለውን ትንሽ ገንዘብ ቆጥቦ ውጤታማ በሆነ ነገር ላይ እንዲውል የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባችሁ ለማስገንዘብ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ሀጂ ኢብሳ አክለውም በዚህ ዓመት ከተመደበው በጀት 65 በመቶ የሚሆነው የሚውለው ለግዥ አገልግሎት ሲሆን ከዚህ ውስጥ በሀገር ደረጃ ከሚመደብ በጀት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ዩኒቨርሲቲዎች እና ትምህርት ሚኒሲቴር ነው ብለዋል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አደም ፋራህ ከዚህ የምክክር መድረክ የሚገኙ ግብዓቶችን እንደ ዩኒቨርሲቲ መጠቀምና እንደ ሀገርም ለሌሎች ተቋማት የሚጠቅሙ ሀሳቦችን ይዞ በቀጣይ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ከምክክር መድረኩ የሚገኙ ግብዓቶችን በአግባቡ በማደራጀት በቀጣይ እንደሀገር በግዥ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እና የግዥ ስርዓቱን ለማዘመን ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡
 
“የመንግስት ግዥ አፈጻጸም ከልዩ ፈቃድና የተማሪዎች ምግብ አንጻር የሚታዩ ተግዳሮቶች ”በሚል ርዕስ በአቶ ገብያው ይታይህ የመንግስት ግዥ እና ንብረት ባለስልጣን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ “በመንግስት ግዥ የአቤቱታና ጥፋተኝነት አፈጻጻም” በአቶ ደምሱ አብዲ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአቤቱታ እና ጥፋተኝነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ “የህጋዊነት ኦዲት አፈጻጸም የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች” በአቶ አዲስ ጎዳና የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኦዲት እና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ “ግዥ ለአካባቢ እና ለዘላቂ ልማት” በዶ/ር ማቴዎስ እንሰርሙ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዚዳንት፣ “በከፍተኛ ትምህርት የግንባታ ግዥና ውል አስተዳደር የሚስተዋሉ ችግሮች” በዶ/ር ተመስገን ወንድሙ ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ “በዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክት አስተዳደር ተግዳሮቶች” በአቶ ማተቤ ከኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን እና “ዘመናዊ የንብረት አስተዳደርና የነዳጅ አጠቃቀም” በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተሰኙ ጽሑፎች ለውይይት ቀርበዋል፡፡
 
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ማጠቃለያ የሰጡት የኤፌዴሪ ትምህርት ሚኒሲቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ለግዥም ሆነ ለፋይናንስ ህግ ያስፈልገናል ሲሉ፤ የህጉ ዓላማ ግን ተቋምን ለማሰር መሆን የለበትም፤ ይልቁንም ተቋም ሰርቶ፣ ተልዕኮ አሳክቶ ሀገር የሚቀይር የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ አክለውም ኦዲትን በተመለከተ የክዋኔም፣ የግዥም፣ የፋይናንስም ኦዲት ሲደረጉ የሀገር መገለጫ ይሆናል፣ የተቋማት መሻሻል የሀገር መሻሻል ነው፡፡ ኦዲቶች ከመሰረተ ሀሳብ ጋር መያያዝ አለበት ፎርሙን ብቻ ተከትለን መሆን የለበትም ብለዋል፡፡
 
በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲው ያሉ የተለያዩ ግቢዎች የምድረ-ግቢ እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የተጎበኙ ሲሆን ጎብኝዎችም በጉብኝታቸው ጽዱ፣ ውብና ማራኪ ስራዎች በዩኒቨርሲቲው መሰራታቸውን በማየታቸው መደሰታቸውንና ወደየ ዩኒቨርሲቲአቸው ሲሄዱ የወሰዱትን ልምድና ተሞክሮ ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ-BDU
ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ
Wisdom at the source of Blue Nile
Thank you for visiting our