ጉዳት ከደረሰባቸው የህልውና ዘማቾች ጋር የዘመን መለወጫ በዓልን አከበረ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀገርን ከወራሪው ለማዳን ሲፋለሙ ጉዳት ከደረሰባቸው የህልውና ዘማቾች ጋር የዘመን መለወጫ በዓልን አከበረ

የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ ከአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ጋር ሲፋለሙ ጉዳት ከደረሰባቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሀይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ አባላት ጋር በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከፍተኛ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እና የህክምና ባለሙያዎች በተገኙበት የማዕድ መጋራት መርሃ-ግብር ተካሄደ፡፡

በስነ ስርዓቱ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የጉዳት መጠናችሁ ቢለያይም ለሀገራችሁ ስትሉ መስዋት ለመሆን መዘጋጀታችሁን በተግባር አሳይታችሁናልና ታላቅ አክብሮት አለኝ ብለዋል፡፡ የሰው ልጆች ስንባል እንቆቅልሽ ነን በአንድ በኩል ምንም ያላጠፋን ምንም ያልበደለን ህዝብ ለመግደል ዝግጁ የሆኑ ሰዎች፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሚወዷችሁ ቤተሰብ እያላችሁ ህይወታችሁን ለዚህ ህዝብ እና ለዚህ አገር ለመስጠት ዝግጁ የሆነ ሰራዊት አለ ሲሉ የልዩነቱን ጥግ አሳይተዋል፡፡ አያይዘውም በክርስትና እምነት ትልቁ የፍቅር መገለጫ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል ህይዎቱን አሳልፎ መስጠቱ መሆኑ እንደሚታመን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ለሀገሩና ለህዝቡ መስዋት የሚሆነው ወታደር ፍቅር መለኪያው ምን ይሆን ሲሉ ለሀገሩ የሚዋደቀውን ወታደር የስብእና ክፍታ አሳይተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሀገራዊ ጥሪው ዙሪያ እያደረገ ስላው እንቅስቃሴ የተናገሩት ዶ/ር ፍሬው አሁን ባለው ሁኔታ መድሀኒቶችንና ባለሙያዎችን ግንባር ድረስ በመላክ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳቶችን ለማከም በአስሩ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ፎረም አማካኝነት በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ፡፡ በመሆኑም ለ30 ዓመታት አብረን እንዳንኖር የተሰራውን ያህል አሁን ላይ የኢትዮጰያዊያን አንድነት የመጣበት ጊዜ በመሆኑ የሰራዊት አባላት ልትኮሩና ደስ ሊላችሁ ይገባል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው በመጨረሻም በቦታው ለተገኙት የሰራዊቱ አባላት ባስተለለፉት መልዕክታቸው በጀመራችሁት ጀግንነት እኛም የኋላ ደጀን በመሆን 2014 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የሚገባትን ሰላም እና አንድነት የምናስቀጥልበት ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው በበኩላቸው ለሀገራችን እና ለማህረሰባችን ህልውና ሲሉ እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እና ጉዳት የደረሰባቸው የመከላከያ ሰራዊት፣ ከክልሎች የተወጣጡ የልዩ ሀይል፣ የፋኖ እና ሚሊሻ አባላት በጥሩ ስነ ልቦና በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ እና ተስፋ እንዲያደርጉ በማሰብ መርሃ-ግብሩ እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡

በበዓሉ ከታደሙት መካከል ከተከዜ ልዩ ሀይል ብርጌድ የሆኑት ዋና ሳጅን አሰሜ አሰፋ እንዳሉት ቆስለው ወደ ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከመጡ ጀምሮ አመራሩ እና የህክምና ባለሙያዎች በዓላት ሳይቀር ቤተሰባቸውን ትተው ላደረጉላቸው ሙያዊ እገዛ እና እንክብካቤ በህልውና ዘማቹ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡