የISSD ፕሮጀክት

በሙሉጌታ ዘለቀ
የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የISSD ፕሮጀክት የእስካሁኑን የስራ ክንውን በደብረ ታቦር ከተማ ገመገመ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------
የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የISSD ፕሮጀክት በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሆኖ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን፣ የመስክ ጉብኝትና የስራ ግምገማ በደብረ ታቦር ከተማ አካሄደ፡፡

የጋራ ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ም/ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ሲሆኑ የተቀናጀ የሰብል ዝርያዎች /ምርጥ ዘር/ ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትና በዘርፉ የተሰማሩ አካላት አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እንዲጠቀሙ እንዲሁም የምርጥ ዘር እጥረቶችን ለመቅረፍ የISSD ፕሮጀክት ትልቅ አስተዋፆ እያደረገ እንደሆነ ተልፀዋል፡፡ ይህም ለሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ለግብርና ቢሮ አርአያ የሚሆን እና የአርሷደሩን የምርጥ ዘር ክፍተትን የሞላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ምን ያህል ተግባራዊ አንደሆነ መመልከት ብቻ ሳይሆን ሞዴል አርሷደሮች ከፕሮጅክቱ የቀሰሙትን ልምድ በሚገባ ተጠቅመው በትንሽ የእርሻ መሬት ላይ አጥጋቢ ምርት መሰብሰባቸውን ልብ ይሏል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ደረጀ አያሌው እንዳሉት ፕሮጀክቱ አርሶ አደሩን ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን የድንች ዘር በበሽታ እየተጠቃ መምጣቱን ተከትሎ በምርምር የታገዘ በሽታን የሚቋቋም የድንች ቲሹ በማራባት በማህበራት ለተደራጁ ሞዴል አርሶ አደሮች ዝርያውን ከማቅረቡ ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በተግባር በማሳየቱ ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡ በሽታን የሚቋቋምና ጥራት ያለው ዘር አምርቶ ለአርሶ አደሩ በማቅረብና በማዳረስ የህብረት ስራ ማህበራት ሀላፊነት እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን ይህንን ለማሳካትም ፕሮጀክቱ ከአዲስ አለም የዘር ብዜት ግብይት ማህበራት ጋር በመቀናጀት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከበሽታ ነፃ የሆነና ምርታማነቱን በእጥፍ የሚያሳድግ የድንች ዝርያ ለይቶ ማሳያ የISSD ፕሮጀክት ለጋሳኝ እና አካባቢዋ አርሶ አደሮች በስፋት መስራቱን ገልፀዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የISSD ፕሮጀክት እስካሁን ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ፈጠራና ምርጥ ዘርን የማዳረስ ስራን በስፋት መስራቱንና ይህ ፕሮጀክት የስራ ጊዜው ቢጠናቀቅ እንኳን የአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ዩኒቨርሲቲዎቸ /እና አጋር ተቋማት ይህንን በጎ ስራ ማስቀጠል እና አርሶ አደሩን የተለያዮ ስልጠናዎችን በመስጠትም ሆነ ምርጥ ዘር በማቅረብ መደገፍ እንዳለባቸው አፅንኦት ተሰጥቶታል፡፡ ዶ/ር ደረጀ አክለውም በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸው የክልል ተቋማት በቴክኒክ እና በአቅም ግንባታ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ከመስክ ምልከታው የተገኙ ጠንካራና ደካማ ጐኖችን በማንሳት ውይይት የተደረገ ሲሆን የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም ተሳታፊዎቸ አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የመስክ ምልከታው አይን ከፋች እንዲሁም አስተማሪና አበርታች እንደነበር ገለፀው፤ ዩኒቨርሰቲው ከመማር ማስተማሩ ባለፈ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ምርምሮችን እያካሄደ እንደሚገኝ እና እነዚህ የምርምር ውጤቶች ችግር ፈቺ እንዲሆኑና ወደ አርሶ አደሮች እንዲደርሱ በርትተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ስራዎች ሲሰሩ የአርሶ አደሩን ህይወትና የአኗኗር ሁኔታ በማገናዘብ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ፕሬዚደንቱ ይህንን ፕሮጀክት የማስቀጠል ስራ የዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም የበኩላቸውን ሚና መጫዎት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ምርጥ ዘርን በተመለከተ አምራች ማህበራት በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ማዳረስ እንዳለባቸውና በወቅቱ ለማያደርሱ ማህበራት የተጠያቂነትን አሰራር መምጣት እንዳለበት በአፅዕኖት ተናግረዋል፡፡

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የISSD ፕሮጀክት ጋር አብሮ በመስራቱ የተገኙ ጥሩ ተሞክሮዎችን የፎቶ ግራፍ አውደርይ በማዘጋጀት ለተሰብሳቢዎች አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ም/ኃላፊ እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንትን ጨምሮ ምክትል ፕሬዚደንቶችና ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል፡፡