የፀኃይ ግርዶሽ ምልከታ

የኢትዪዺዽያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የባህርዳር ቅርንጫፍ እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዋሸራ ጅኦስፔስና ራዳር ሳይንስ የምርምር ላቦራቶሪ በጭስ አባይ የፀኃይ ግርዶሽ ምልከታ አካሄዱ
--------------------------------------------------------------------------------------------
በቦታው ስለነበረው ሁኔታ እና ስለፀሀይ ግርዶሽ ጠቅለል ያለ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የዋሸራ ጅኦስፔስና ራዳር ሳይንስ የምርምር ላቦራቶሪ ዳይሬክተር ዶ/ር መልሰው ንጉሴ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡
በቦታው ከ12፡20 ጀምሮ በመገኘት እስከ 3፡00 ድረስ ክስተቱን የጨረር መነጸር(solar glass) በመታገዝ ይከታተሉ እንደነበርና የኢትዪዽያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከቦታው በቀጥታ ስርጭት ይልክ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
 
ክስተቱ በአብዛኛው ኢትዮዽያ በተለይም በሰሜን እና ምዕራብ ኢትዮዽያ የተከሰተ መሆኑን አስታውሰው የግርዶሹ አይነት ከፊል(Partial solar eclipse) እና ቀለበታማ( annular solar eclipse) የፀኃይ_ግርዶሽ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡
ስለክስተቱ ምንነት እና አፈጣጠር ሲያብራሩ መሬት በፀሀይ ዙሪያ ስትዞር እና ጨረቃ በመሬት ዙሪያ ስትዞር መሬት፣ ፀሀይ እና ጨረቃ ትይዩ(In a straight line) በሚሆኑበት አጋጣሚ፤ ጨረቃ በመሬት እና በፀሀይ መካከል በመሆን ከፀሀይ የሚመጣውን ጨረር ስታግደው የጨረቃ ጥላ መሬት ላይ ያርፈና የፀኃይ ግርዶሽ ይፈጠራል ብለዋል፡፡
 
የአሁኑ ግርዶሽ ጨረቃ ከመሬት በጣም እርቃ በምትገኝበት ወቅት የተከሰተ ስለሆነ ጨረቃ ሙሉ በሙሉ ፀሀይን ማገድ ስለማትችል ነው ቀለበታማ ግርዶሽ የተፈጠረው ይላሉ፡፡ ሙሉ ግርዶሽ የሚፈጠረው ጨረቃ ለመሬት በጣም ቅርብ በምትሆንበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡
 
በአለም በየዓመቱ ከ2 እስከ 5 የሚደርስ የፀሀይ ግርዶሽ እንደሚከሰት ጠቁመው
ግርዶሹን ለመመልከት የሚያስችል ከመቶ(100) በላይ የጨረር መነጸር (solar glass) ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መሰጠቱን ዳይሬክተሩ አክለው ተናግረዋል፡፡