የዘንዘልማ ግቢ ሰራተኞች ድጋፍ

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዘንዘልማ ግቢ ሰራተኞች ለአማራ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ አባላት ከደሞዛቸው በማዋጣት ድጋፍ አደረጉ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዘንዘልማ ግቢ የሚሰሩ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ህግን በማስከበር ሂደት ጉዳት ለደረሰባቸው ለጅግናው አማራ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ አባላት ከደሞዛቸው ከ30-100 ፐርሰንት በማዋጣት 477,759 ብር የሚያውጣ ድጋፍ በማድረግ አብሮነታቸውን አሳይተዋል። ድጋፉ የተደረገው በአይነት ሲሆን በእለቱ የተበረከቱትም ፒጃማ፣ አንሶላ፣ ፎጣ፣ ነጠላ ጫማ፣ አውቶማቲክ የልብስ ማጠቢያ ማሽን (18ኪ/ግ)፣ 55 ኢንች ቴሌቪዥን ፣ የቴሌቪዥን ዲኮደርና ዲሽ፣ 2 ኩንታል ገብስ፣2 ኩንታል አጃ፣ ለዓመት በዓሉ የሚሆን በግ፣ መነፅር፣ 8 የአካል ጉዳት ለደረሰባችው ሰዎች አጋዥ መሳሪያዎች ናቸው።

ዶ/ር አሳምነው ጣሰው በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይኝስ ኮሌጅ ዲን እንዳሉት ሁሉም ሰው በሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ለሚገኙ እና በሰላም ማስከበር ሂደት ጉዳት ለደረሰባቸው የፅጥታ አካላት፣ ለተፈናቅሉ ወገኖች፣ ለዓቅመ ደካሞች በአጠቃላይ ደጋፍ ለሚሹ አካላት ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ቢወጣ መልካም ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አንዱ የሆኑት ዋና ሳጅን ማንደፍሮ አለባቸው በበኩላቸው ለተደረገላቸው ነገር ሁሉ ምስጋና በማቅረብ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዘንዘልማ ግቢ የሚሰሩት መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ያሳዩት የአብሮነትና መተሳሰብ እሴት ሁሉም ባህል ሊያደርገው የሚገበ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።