የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ችግኝ ተከላ

በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በባሕር ዳር ቤዛዊት ተራራ ላይ ችግኝ ተከላ አካሄዱ
======================================================
በሙሉጌታዘለቀ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ "የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለል፣ የአባይን ወንዝ እና የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ እንታደግ” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የባህር ዳር ከተማ ም/ከንቲባን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በቤዛዊት ተራራ የችግኝ ተከላ ተካሄደ፡፡

በመርሀ ግብሩ የባሕር ዳር ከተማ ም/ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለከተማዋ እስትንፋሷ መሆኑን አውስተው፣ የጣናንና አባይን ህልውና ለማስቀጠልና ከደለል ለመታደግ ተቋማት በያሉበት ችግኞችን በመትከል የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በተካታታይ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ ዶ/ር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው ችግኞች ፀድቀው ለተፈጥሮ ሐብት ጥበቃና ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያለሙዋቸው ቦታዎች ህብረተሰቡን በባለቤትነት ያሳተፈ መሆን እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ሲናገሩም በጉና ተራራ የተጀመረው የዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢ ጥበቃ ስራ በጮቄ ተራራ ቀጥሎ ባህር ዳር በቤዛዊት ተራራ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ጉዞውን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ችግኞች መፅደቃቸውን መከታተልና የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲሆኑ ማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚጠበቅ ጠቁመው የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ አንፃር ተከታታይ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

አክለውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የላንታና ካማራ /የረኛ ቆሎ/ አረምን ከማስወገድ ጀምሮ በርካታ የልማት ስራዎችን ከሶሳይቲ ፎር ኢኮቱሪዝም እና ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በቀጣይም በተራራው የኬብል ካር ቴክኖሎጂን በመዘርጋት ለተማሪዎች አገልግሎት የማዋል እቅድ እንዳለው ጠቅሰው በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የአማራ ክልል አመራሮች ባሉበት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአባይ ወንዝ ላይ ያወጣውን የአቋም መግለጫ አቅርበዋል፡፡

አመራሮች ከችግኝ ተከላው በፊት ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል /STEM Center/ አጫጭር ስልጠና የሚሰጥበትን ተቋም እና የደንገል ልማት ፕሮጀክት ስራዎችን መጎብኘታቸው ታውቋል ፡፡