የአልባሳት ድጋፍ ለቆሰሉ የፀጥታ ኃይሎች

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን በጦርነቱ ለቆሰሉ የፀጥታ ኃይሎች የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ

***************************************************************************

(ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፤ታህሳስ 27/2014ዓ/ም)

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሶሻል ሳይንስ ፋኩሊቲ መምህራን 14‚300 (አስራ አራት ሺህ ሶስት መቶ)ብር በማዋጣት በፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ቁስለኞች ማገገሚያ ማዕከል ለሚታከሙ የመከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሀይልና ፋኖ አባላት የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡

ታካሚዎችን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት የማገገሚያ ማዕከሉ ኃላፊ ኮማንደር ታደሰ ሹምዬ በአሁኑ ሰዓት ታካሚዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዉ፤ ለዚህም በማዕከሉ የሚሰሩ ሀኪሞች በኢትዮጱያዊነት ስሜት ሌት ተቀን በመስራታቸዉ ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡

ኮማንደር ታደሰ አክለዉም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማገገሚያ ማዕከሉን ህንፃና ቤተ መፃህፍቱን ሰርቶ በመስጠት ሀገራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዉ ውስጥ እያስተማሩ ያሉ መምህራንም ከሙያዊ ድጋፍ በተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸዉ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ገልፀዉ ሌሎች አካላትም ከአልባሳት በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የክራንች፣ የዊልቸርና መሰል ቁሳቁሶች እጥረት ስላለብን ድጋፍ እንዲያደርጉልን ሲሉ ጥሪ  አቅርበዋል፡፡

በሶሻል ሳይንስ ፋኩሊቲ የሶሻል ወርክ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ መለሰ የትምህርት ክፍላቸዉ በወቅታዊ ሀገራዊ ችግር ምክንያት የስነ- ልቦና፣የማህበራዊና የጤና ችግር ለደረሰባቸዉ አካላት ድጋፍ ለማድረግ ከሌሎች ትምህርት ክፍሎች ጋር በመሆን እየሰሩ መሆኑን ገልፀው፤ ለሀገር ሲሉ ህይወታቸዉን እየሰጡ ለሚገኙ ዘማቾች አቅማችን የፈቀደዉን ያህል ገንዘብ በማዋጣት የአልባሳት ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ከባለሀብቶች፣ከበጎ ፈቃደኞች፣ ከስነ-ልቦና እና ስነ-አዕምሮ ባለሙያዎች ጋር በመሆን አስፈላጊዉን  ድጋፍ ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድጋፍ የተደረገላቸዉ ታካሚዎችም ጉዳታቸዉን በመጎብኘት ድጋፍ እያደረጉላቸዉ ለሚገኙ አካላት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

ዘጋቢ፡- ሸጋው መስፍን