የተማሪዎችን አቀባበል ...

የተማሪዎችን አቀባበል በተመለከተ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ተካሄደ

***************************************************************

   (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፤ታህሳስ 27/2014ዓ/ም)

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በተከሰተው የህልውና ጦርነት ምክንያት አቁሞ የነበረውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል በሁሉም ግቢዎች የሚገኙ የተማሪዎች አገልግሎት ሰራተኞችን ታህሳስ 27/2014 ዓ.ም በጥበብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አደረገ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን ዶ/ር ምኒችል ግታው ከተለያዩ ቦታዎች ለትምህርት የሚመጡ ተማሪዎች በወቅታዊ ጉዳዩ ምክንያት የስነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው፣ የኢኮኖሚ ችግር የገጠማቸው እና በችግሩ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ተማሪዎች ቢኖሩ ሊያጋጥማቸው ስለሚችለው የስነ-ልቦና እና ተያይዞ ስለሚመጣው የስነ-ምግባር ጉድለት ልዩ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል በማለት ለተወያዮች በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ጥራት አስተዳደር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አንዳርጋቸው ሞገስ ጦርነቱ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ያስከተለ በመሆኑ የሚመጡት ተማሪዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንደቤተሰብ በመሆን ከድሮው በተለየ መልኩ ለሚያጋጥሙ ችግሮች የመፍትሄ አካል ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ሰዓት በተለይ የስነ-ምግባር መርሆች ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ሰፊ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በመጨረሻም የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ፍቅሬ አልማው ከተወያዮች የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን በመቀበል የውስጡን ችግር እየፈታን ዩኒቨርሲቲው የእኔ ነው ብለን በጋራ ተጋግዘን፣ ተወያይተን መስራት እና የሚመጡትንም ተማሪዎች በፍቅር እና በጥሩ አቀራረብ ልናስተናግዳቸው ይገባል በማለት ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ባንቹ ታረቀኝ