የቆዳና የአልባሳት ምርቶችን ለኤግዚቪሽን አቀረበ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ተቋም የቆዳና የአልባሳት ምርቶችን ለኤግዚቪሽን አቀረበ

******************************************************************

በባሕር ዳር ከተማ አለ በጅምላ ግቢ በተዘጋጀው የትንሳኤ እና የኢድ ዋዜማ የንግድ ትርኢትና ባዛር ላይ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ተቋም በተማሪዎች ዲዛይን የተደረጉ የቆዳና የአልባሳት ውጤቶችን ለእይታ አቅርቧል፡፡

በኤግዚቪሽኑም ከቆዳና ከጨርቃ ጨርቅ የተሰሩ ጃኬቶች፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች፣  የህፃናት  ማዘያና  መሰል  ምርቶች ለእይታ ቀርበዋል፡፡

ምርቶቹን ሲመለከቱ ያገኘናቸውና ስለምርቶቹ አጠቃላይ ሁኔታ የጠየቅናቸው ዶ/ር ፀሐይ ነጋ እንደነገሩን አልባሳቱ ለተለያየ ዓላማ  እንድንጠቀምባቸው ታስበው በመሰራታቸው ለአጠቃቀም ቀላልና ምቹ ናቸው ብለዋል፡፡ ዲዛይነሮቹ በደንብ ቢታገዙ፣ ቴክኖሎጂው ቢሻሻልና የተሻለ ስልጠና ቢሰጥ ከዚህ የተሻለ ነገር እንደሚሰራ አምናለሁ ብለዋል፡፡ ዶ/ር ፀሐይ አክለውም ምርቶች ላይ ስራ ከመስራታችን አስቀድሞ አመለካከት ላይ መሰራት አለበት ያሉ ሲሆን ምርቶች የትም ሀገር ይመረቱ መታየት ያለበት ጥራታቸው ነው፤ ስለሆነም በሀገራችን ተወዳዳሪ ምርት በማምረት ልክ ህንድን እንደመሰሉ ሀገራት የሀገራችንን ምርት መጠቀም ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡን አቶ ጌታሁን ስዩም ይባላሉ፡፡ ከባሕር ዳር  ከተማ  እንደመጡ ነግረውን  የተሰሩት ስራዎች በጣም ጥሩዎች መሆናቸውን ገልፀው፤ ሆኖም የኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲኖር ዩኒቨርሲቲው ከባለሀብቶች ጋር በጋራ መስራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ አክለውም ተማሪዎችን በሚገባ ማብቃትና ትልልቅ ማሽኖችን መጠቀምም ስራውን የበለጠ ለማዘመን ያግዛል ብለዋል፡፡

ምርቶቹን ለተመልካቾች በማቅረብ የማስተዋወቅ ስራ እየሰሩ ያገኘናቸው ወ/ሮ ኑኑሸት ምትኩ ህብረተሰቡ ጥሩ አስተያየት እየሰጠ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ይሁን እንጂ ምርቶቹ ለሽያጭ መቅረብ እንዳለባቸው ብዙ አስተያየት ሰጭዎች እንደነገሯቸው አክለው ገልፀውልናል፡፡