የሴቶች ቀን

ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን በዩኒቨርሲቲው ተከበረ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ፆታና ልማት ጥናት ት/ክፍልና የስርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ቢሮ በጋራ በመተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ ለ43ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሴቶች ቀን “National-all women conference on women in academia” በሚል መሪ ቃል  በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተካሄደ ውይይት አክብረዋል፡፡

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ዩኒቨርሲቲው ሴቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉትን ሴት መምህራን፣የአስተዳደር ሰራተኞችና ተማሪዎች ማግኘት የሚገባቸውን ድጋፍና ክትትል እንዲያገኙ የስርዓተ ፆታ ቢሮ ውግንናውን እንዲያሳይ በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮውን የሴቶች ቀን አከባበር የተለየ የሚያደርገው ከሴቶች ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተያያዥ ግንኙነት ያላቸው በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ፍያማ ውይይቶች መደረጋቸው ነው፡፡ የፓናል ውይይቱን ያካሄዱትና ጥናታዊ ፅሁፎችን ያቀረቡት ከተለያዩ ተቋማት ተጋብዘው የመጡ እንግዶችና የዩኒቨርሲቲው ሴት ምሁራን ናቸው፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ ጉልተው የታዩት ሀሳቦች ሴቶችን የማብቃት ዘዴ ምን እንደሚመስል፣ፖሊሲዎች እንዴት እንደሚቀረፁና እንደሚተገበሩ እንዲሁም ለወደፊቱ ሴቶችን ከጥቃት ለመታደግ ምን መደረግ እንደሚገባ የሚያስገነዝቡ እና ሌሎች የሴቶች ንቃተ-ህሊና እና አቅም ማሳገግ ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡

Date: 
Saturday 12, 2019
place: 
Bahir Dar University
March, 2019